አረብ ኤምሬትስ ሱልጣን አል ጀበርን የ28ተኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ፕሬዝዳንት አድርጋ ሾመች
የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በፈረንጆቹ ህዳር 2023 በአረብ ኤምሬትስ ይካሄዳል
ሀገሪቱ ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ጉባኤውን የሚያሰናዱና የሚያስተባብሩ የስራ ኃላፊዎችን መድባለች
አረብ ኤምሬትስ ሱልጣን አል ጀበርን የ28ተኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 28) ፕሬዝዳንት አድርጋ መሾሟን አስታውቃለች።
የሱልጣን አል ጀበርን ሹመት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና በሼክ መንሱር ቢን ዛይድ አል ናህያን ውሳኔ መሰረት ነው የተሰጠው ተብሏል።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ሚንስትር ሼክ ማንሱር ቢን ዛይድ አል ናህያን ሱልጣን አል ጀበርን እንዲሾሙ ዛሬ ውሳኔ አሳልፈዋል።
የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሻማ ቢንት ሱሃይል ቢን ፋሪስ አል ማዝሮኢ ደግሞ በጉባኤው የወጣቶች የአየር ንብረት መሪ፤ ራዛን አል ሙባረክ ደግሞ የዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ ህብረት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመድበዋል።
የስራ ኃላፊነቱ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰባት ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ፣ የብዝኸ ህይወት መጥፋት እና የኃይል አቅርቦት የማረጋገጥ ተግዳሮቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሚካሄደው የኮፕ 28 ጉባኤ ዝግጅት አካል ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ታዳጊ ሀገራትን፣ ያደጉ ሀገራትን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን እና የግሉ ዘርፍን ጥረቶችን አንድ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ እርምጃዎችን በማጠናከር ላይ ትገኛለች ተብሏል።
በአየር ንብረት እርምጃዎች ውስጥ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን እና ዝቅተኛውን የምርት ወጪን በመቀበል ወደ ንጹህ ኃይል ለመሸጋገር በምታደርገው ጥረት በአየር ንብረት እርምጃ የመሪነት ሚና አላትም ተብሏል።
ሀገሪቱ በ70 ሀገራት ለታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ መወዕለ-ነዋይ እንዳፈሰሰች ተነግሯል።
በዓለም ዙሪያ በፈረንጆቹ እስከ 2030 ተጨማሪ 50 ቢሊዮን ዶላር ለማፍሰስ አቅዳለች።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የፓሪስን የአየር ንብረት ስምምነት በመፈረም እና በማጽደቅ፣ ልቀቶችን በመቀነስ እና በ2050 የአየር ንብረት ገለልተኝነትን ለማሳደድ ያላትን ስልታዊ ተነሳሽነት አስታውቃለች።
በዚህ "ወሳኝ" አስር ዓመታት ውስጥ ለአየር ንብረት እርምጃ የፍላጎት ጣሪያን ከፍ ለማድረግ ቃል ተገብቷል ።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እርምጃ ያላትን ቁርጠኝነት ጉባኤውን በማሰናዳት ትልቅ ቦታ ትሰጣለች ተብሏል።
ሀገሪቱ ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ የስራ ኃላፊነት ድልድል አውጥቻለሁ ብላለች።