ኢትዮጵያን ጨምሮ 4 የአፍሪካ ሀገራት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ የመጀመሪያ ሰዎች መገኘታቸውን ዛሬ ሪፖርት አድርገዋል
ኢትዮጵያን ጨምሮ 4 የአፍሪካ ሀገራት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ የመጀመሪያ ሰዎች መገኘታቸውን ዛሬ ሪፖርት አድርገዋል
በቫይረሱ የተያዘው የካቲት 25/2012 ዓ.ም ከቡርኪናፋሶ ወደ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ የመጣ የ48 ዓመት ጃፓናዊ ነው። በጉዳዩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ መግለጫ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ከበሽተኛው ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦችንም የመለየትና ክትትል የማድረግ ስራ ተጀምሯል፡፡ ችግሩን ለመከላከል 300 ሚሊዮን ብር በመንግስት ተመድቧል፡፡
ኬንያም ኮሮና ወደ ሃገሯ መግባቱን አረጋግጣለች፡፡ ወረርሽኙ ከአሜሪካ በመጣች አንዲት ኬኒያዊት ላይ እንደተገኘ መረጋገጡን የሃገሪቱ ካቢኔ የጤና ጉዳዮች ዋና ጸሃፊ ሙታሂ ካግዌን ዋቢ አድርጎ ዴይሊ ኔሽን ዘግቧል፡፡
ጋቦንና ጋና ኮሮና ቫይረስ ወደ ሃገራቸው መግባቱን ያረጋገጡ ሌሎች የሰሃራ በታች ሃገራት ሆነዋል፡፡ ቫይረሱ ሰሞኑን ከአውሮፓ በተመለሱ ዜጎቻቸው ላይ መታየቱን ሁለቱም ሃገራት አረጋግዋል፡፡
ይህም ወረርሽኙ የተገኘባቸውን የአፍሪካ ሃገራት ቁጥር ወደ 15 ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ ባየቃላይ ከ 100 በላይ የቫይረሱ ታማሚዎች በአፍሪካ የሚገኙ ሲሆን ግብጽ ከ80 በላዩ የሚገኙባት ግብጽ ነች፡፡
ሱዳን በኮሮና ቫይረስ ስጋት ከግብጽ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር ዘጋች
ሱዳን ከ 8 ሀገራት ጋር የምታደርገውን በረራ ማቋረጧንና ከግብጽ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር መዝጋቷን አስታውቃለች፡፡
የሱዳን ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዳይሬክተር ጄነራል ኢብራሂም አድላን ለ ሱዳን ትሪቡን እንዳሉት ወደ ኮሪያ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ጣሊያን፣ ኢራን፣ ስፔን፣ ግብጽና ፈረንሳይ እዲሁም ከነዚህ ሃገራት ወደ ሱዳን የሚደረጉ በረራዎች እንዲቋረጡ ተወስኗል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ መሆኑን ያስታወቀው የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱን በወረርሽኝነት መፈረጁ የሚታወስ ነው፡፡
በዓለም ዙሪያ እስካሁን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ132,500 በላይ ሲደርስ 5,000 ያክል ሰዎች ሞተዋል፡፡
የተለያዩ ምንጮችን ለዘገባው በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡