ምርምሩ ገና በጅምር ላይ ያለ በጨቅላነትም ሊጠቀስ የሚችል እንጂ የተረጋገጠ ነገር የለውም- ፋርማኮሎጂስት መንሱር ሻፊ
የወባ መድኃኒቶች ኮሮናን ፈዋሽነት እስከምን ድረስ?
መላው ዓለምን በማስጨነቅ ላይ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መድሃኒት እንደተገኘለት ሆኖ ከሰሞኑ እየተወራ ይገኛል፡፡ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች ጭምር ሳይቀሩ ይህንኑ ሃሳብ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ በተለይም በወባ በሽታ መከላከያነታቸው የሚታወቁት ክሎሮኪን እና ሃይድሮክሲ ክሎሮኪን እንዲሁም አዚትሮማይሲን የተባሉ መድሃኒቶች ከቫይረሱ ለፈውሱ እንደሚችሉ ሲዎራ ሰንብቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ ስለዚሁ ጉዳይ በየማህበራዊ ገጾቻቸው ሲያጋሩ ሲያወሱ የተመለከትናቸው ሰዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ ሙከራውን “ማርሽ ቀያሪ”ም ብለውታል፡፡
እውነት ነው መድሃኒቶቹ ቫይረሱን ሊያድን የሚችል አቅም ሊኖራቸው እንደሚችል ታሳቢ ያደረጉ የምርምር ስራዎች ቻይናን ጨምሮ በተለያዩ የመመራመር አቅሙም አጋጣሚውም ባላቸው ፈረንሳይን መሰል ሃገራት በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡
ሆኖም የተባለውን ተከትሎ መድኃኒቶቹን ለመጠቀም የሞከሩ የተጠበቀውን እንዳላገኙ ይልቁንም እስከ ሞት ያደረሰ ችግር እንደገጠማቸው በአህጉራችን አፍሪካ ጭምር ሰምተናል፤ ተዘግቦም አይተናል አንብበናልም፡፡
ይህንኑ ታሳቢ አድርገንም ስለ ጉዳዩ ስለ ተባሉት መድኃኒቶች እና ሰጡ ስለተባለው ተስፋም ባለሙያን እናጠይቃለን እስከመጨረሻው ይከታተሉን፡፡
መድኃኒቶቹ ለምን ተስፋን ሊያጭሩ ቻሉ?
ኮሮናን በተመለከተ እስካሁን ተገኘ የተባለ መድኃኒት ወይም ክትባት የለም፡፡ ከወረርሽኙ መጠበቅ የሚቻልባቸውን መንገዶች ከማመላከት ውጪም ያድናል በሚል የቀረበ ተጨባጭ የፈውስ ሃሳብ የለም፡፡ ጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ቢሆኑ ይህንኑ ነው ያረጋገጡት፡፡
ስለ ወባ መድኃኒቶች ኮሮናን ፈዋሽነት አል ዐይን አማርኛ በስልክ ያማከራቸው በቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ የፋርማሲ ባለሙያና ፋርማኮሎጂስት (ረዳት ፕሮፌሰር) መንሱር ሻፊ ዘርዘር ያሉ ሙያዊ ትንታኔዎችን ሰጥተውናል፡፡
በመድሃኒቶቹ ላይ በመካሄድ ላይ ያለውን የምርምር ሂደት ሲያስቀምጡም በህክምናው ዓለም “re purposing” የሚባል ነገር አለ ይላሉ አንድ የነበረ ወይም ለአንድ የህመም ዓይነት ሲያገለግል የነበረ መድሃኒት በአጋጣሚ፣በልምድ ወይም በምርምር ሌላ በሽታን ሊያድን የሚችልበትን ሁኔታ ለመጠቆም፡፡ ይህ ካለው ነገርና ልምድ የሚገኝ ነው፡፡
ክሎሮኪንም ካንሰርን ጨምሮ ለተለያዩ ጸረ-ማቃጠል ተብለው ለተለዩ መድሃኒቶች (anti-inflammatory drugs) መፍትሄ ይሆን እንደሆነ በሚል የሚደረጉ ሙከራዎች እንዳሉም ይገልጻሉ፡፡
ከ70 በላይ ኬሚካሎች በሙከራ ላይ ናቸው የሚሉም ሲሆን የዓለም የጤና ድርጅትም 5 አካባቢ መድሃኒቶችን እየሞከረ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ኮሮናን እንደሚፈውሱ የተነገረላቸው መድኃኒቶች ላይ እየተካሄደ ነው የሚባልለት ሙከራ ግን ጅምር እንጂ ውጤት የተገኘበት አይደለም እንደ ባለሙያው ገለጻ፡፡
ሙከራው በእውነት ተስፋ ሰጪ ነው?
ባለሙያው ሙከራዎቹን ገና በጅምር ላይ ያሉ በጨቅላነትም ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው እንጂ የተረጋገጠ ነገር የለም ይላሉ የትኛውም መድሃኒት ወደ ገበያ ከመውጣቱ በፊት የሚያልፋቸው ብዙ ደረጃዎች እንዳሉ በመጠቆም፡፡
ቅድመ ክሊኒካዊ (Pre clinical) ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊትም የመድኃኒቱን አጠቃላይ ሁኔታ ሞለኪዩላዊ ባህሪ የጎንዮሽ ጉዳት ጭምር ይጠናል፡፡ የጎንዮሽ ጉዳት አለው የለውም የሚለው በእንስሳት ላይ ከተረጋገጠም በኋላ በተለያየ ደረጃ ሊጠቀሱ በሚችሉ ሂደቶች ውጤታማነቱ በበጎ ፈቃደኞች ከዚያም በታማሚዎች ላይ ይሞከራል፡፡
ሆኖም ቀደም ሲል የተጠቀሱት መድኃኒቶች ገበያ ላይ የነበሩ በመሆናቸው ስለ አጠቃላይ ስሪትና ሁኔታቸው ብዙ ሳይጠና ቀጥታ ደረጃ 2 ተብሎ ወደሚጠራው ብዙም ሳይበዛ ከ100-250 በማይበልጡ ሰዎች ውጤታማነቱና ጉዳቱ ሊሞከር ወደሚችልበት ደረጃ ነው የገባው እንደባለሙያው ገለጻ፡፡ይህ ግን በሙከራ ደረጃ እንጂ ሊያድን እንደሚችል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችል አይደለም፡፡
ህመም ባለባቸውና በሌለባቸው ሰዎች ላይ፤ በሆስፒታሎች በሌሎች የህክምና ተቋማትም ጭምር ሰፋ ባለ ሁኔታ ሊሞከር ወደሚችልበት ደረጃ መሸጋገርን ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ አሁን ያለውና የሚባለው ነገር ብዙ መልካም ነገሮች ቢኖሩትም ብዙም ተስፋ ሊጣል የሚችልበት ነገር እንደሌለ አመላካች ነው፡፡
በሚባለው እንዳንዘናጋ ምን ይሁን?
ረዳት ፕሮፌሰሩ የመድሃኒቶቹን ስም ራሱ መጥቀስ አይገባም ይላሉ፡፡ ምናልባትም አጋጣሚውን መጠቀም ለሚፈልጉ አካላት ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር እና ወባ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ያለውን የመድኃኒት አቅርቦት ሊያሳሳው፤ ህብረተሰቡንም ላልተፈለገ ወጪና እንግልት ሊዳርገው እንደሚችልም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
መድኃኒቶቹ የዓለም የጤና ድርጅት ጭምር ምርምር እንዲደረግባቸው ካዘዛቸው መድሃኒቶች መካከል መሆናቸውን የሚናገሩት ባለሙያው አንድን መድሃኒት ወደ ገበያ ለማስገባትና ጥቅም ላይ ለማዋል ቢያንስ በትንሹ ከ15 እስከ 20 ዓመታት ሊወስድ ይችላል በመሆኑም ውጤታማነቱ ተረጋግጧል በሚል ህብረተሰቡ እንዳይዘናጋ ሲሉ ይመክራሉ፡፡
በእንዲህ ዓይነቱ ነገር ከመዘናጋት ይልቅ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ራስን ከቫይረሱ መጠበቅ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
ስለ ጉዳዩ የጠየቅነው ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም መድኃኒቶቹ ህመምን ተከትለው ለሚታዩ ምልክቶች ብቻ እንደሚታዘዝ ገልጾልናል፤መድኃኒቶቹ በጤና ስርዓቱ ውስጥ ከሚገኙ ተቋማት ውጪ የትም እንደማይሸጡ በማከል፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመግታት እንደሚያስችሉ ተስፋ የተጣለባቸው የምርምር ስራዎች ጭምር በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡
የኢንቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ትናንት የባህል እና የዘመናዊ ህክምና አዋቂዎችን በማቀናጀት የተሰራው የኮሮና ቫይረስ መድኃኒት መሰረታዊ የምርምር ሂደቶችን ማለፉን ቀጣይ ወደ እንስሳት እና ክሊኒካል ፍተሻዎች መሸጋገሩን እንዲሁም ለማምረት የሚያስችል ዝግጅትን በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ይህ የሚያበረታታ እና ተስፋን ሊሰጥ የሚችል ነው፡፡ ሆኖም አሁንም ከንክኪ በመራቅ፣ ግለሰባዊ ርቀታችንን በመጠበቅ እንዲሁም ንጽህናችንን በመጠበቅ የህክምና ባለሙያ ምክረ ሃሳቦችንም በመተግበር ራሳችንን ሌሎችንም ሃገራችንንም ጭምር ልንታደግ ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እስከ ትናንት አርብ ድረስ 16 ደርሷል፡፡ ስርጭቱን ለመቆጣጠርም በመንግስት በህብረተሰቡም በኩል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ሁሉ በራሳቸው ወጪ በተመረጡ ሆቴሎች እንዲገለሉና የሃገሪቱ የድንበር በሮችም ተዘግተው እንዲቆዩ በሚኒስትሮች ደረጃ የተቋቋመው ብሄራዊ ምክር ቤት መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡