ቁሳቁሶቹን በ5 ቀናት ውስጥ ነው ለ39 የአፍሪካ ሃገራት አጓጉዞ የጨረሰው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጃክ ማ የተበረከቱ የድጋፍ ቁሳቁሶችን ለ39 የአፍሪካ ሃገራት አጓጉዞ ጨረሰ
የፓን አፍሪካ ምልክት ሆኖ በማገልገል ላይ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጃክ ማ የተበረከቱ የድጋፍ ቁሳቁሶችን ለ39 የአፍሪካ ሃገራት በ5 ቀናት ውስጥ አጓጉዞ ጨረሰ፡፡
በዚህም አየር መንገዱ የአፍሪካ ኩራት እና አለኝታነቱን በዚህ መላው ዓለም እየተፈተነ ባለበት የችግር ወቅት ጭምር በድጋሚ አሳይቷል፡፡
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያም በዚህ ፈታኝ ወቅት የአፍሪካን ህዝብ ለማገልገል አየር መንገዱ ለተሰጠው ዕድል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይንና ጃክማን አመስግነዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ሰጭነት በጃክ ማ ደጋፊነት እና በአጋሮቻችን ትብብር የተላኩትን ቁሳቁሶች በ5 ቀናት ውስጥ አጓጉዘን መጨረሳችንን ስናሳውቅ በታላቅ ደስታ ነው ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
አየር መንገዱ በብዙዎቹ ሃገራት በብቸኝነት ነበር ቁሳቁሶቹን ሲያጓጉዝ የነበረው፡፡
በመጪዎቹ ቀናት እንደሚቀጥል ከሚጠበቀው ድጋፍ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ስለማጓጓዙም አየር መንገዱ አስታውቋል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የተጀመሩ አህጉር አቀፍ ጥረቶችን ለመደገፍ በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አግባቢነት በአሊባባ ፋውንዴሽን የተበረከቱትን ቁሳቁሶች ኢትዮጵያ እንድታከፋፍል መመረጧ የሚታወስ ነው፡፡