መንግስት የታገቱት ተማሪዎች በምን ሁኔታ እንዳሉ እንዲያስታውቅ አምነስቲ ጠየቀ
መንግስት የታገቱት ተማሪዎች በምን ሁኔታ እንዳሉ እንዲያስታውቅ አምነስቲ ጠየቀ
መንግስት ከደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ የታገቱ ሴት የአማራ ተማሪዎችን በተመለከተ ምን እየሰራ እንደሆነ እንዲያስታውቅ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ፡፡
ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት ባሳለፍነው ወርሃ ህዳር የታገቱት 17ቱ ተማሪዎቹ እስካሁን ድረስ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አልታወቀም ያለው አምነስቲ በአካባቢው የስልክና ኢንተርኔት ግንኙነት መቋረጡና ዩኒቨርስቲዎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተማሪዎቻቸውን ማሰናበት መጀመራቸው የታጋች ቤተሰቦችን ይበልጥ እንዳስጨነቀና ጉዳዩ ተዳፍኖ እንዳይቀር እንዳሳሰባቸው መናገራቸውን አስታውቋል፡፡
የአምነስቲ የምስራቅ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሰይፍ ማጋንጎ”የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የፈጠረው ስጋት ከታገቱ 4 ወራት በኋላ እንኳን ስለ ውድ ልጆቻቸው መገኛ ማንን እንደሚጠይቁ የቸገራቸውን የታጋች ቤተሰቦች ይበልጥ አስጨንቋል“ብለዋል፡፡
“መንግስት ዩኒቨርስቲዎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተማሪዎቻቸውን እንዲያሰናብቱ ማድረጉ የሚያስመሰግን ተግባር ነው ሆኖም የታገቱት ተማሪዎች የት እንዳሉ ለማወቅና ከታገቱበት አስለቅቆ ከቤተሰቦቻቸው ለመቀላቀል ጠንከር ያሉ ተመሳሳይ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል“ ሲሉም ነው ያሳሰቡት፡፡
ብዙዎቹን የታጋች ቤተሰቦች ማናገሩን አናግሬያለሁ ያለው አምነስቲ ሆኖም ብዙዎቹ ቤተሰቦች የልጆቻቸው ሁኔታ በተመለከተ የታወቀ ግልጽ ነገር አለመኖሩን ተከትሎ በተስፋ መቁረጥና በደጋፊ እጦት ውስጥ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
ይህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የታጋቾቹን ጉዳይ ተከታትሎ ምላሽ የሚሰጥ እና ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የሚሰራ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ማስታወቃቸውን ተከትሎ የተደረገ ነው፡፡
የ3ኛ ዓመት የባዮቴክኖሎጂ ተመራቂ ተማሪዋ ግርማነሽ የኔነህ ወደ ቤተሰቦቻቸው በማምራት ላይ ሳሉ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት ወላጅ አባቷ አቶ የኔነህ አዱኛ ለአምነስቲ እንደነገሩት ከሆነ
“ወደፊት የተሻለ ህይወት እንደሚኖራቸው በማሰብ ያለንን አሲዘን ልጆቻችንን ወደ ዩኒቨርስቲው ልከናል፡፡ አሁን ግን ይኑሩ ይሙቱ ወዴት እንዳሉም አናውቅም፡፡መታገቷን ነግራን እንደንጸልይላት ከጠየቀችን ቀን አንስቶም እያነባን ነው፤ እንደ ቄስ ሊኬድ ወደሚችልበት የጸሎት ቦታ ሁሉ ሄጃለሁ እናቷ ግን ክፉኛ ተጎድታለች ማበድ ነው የቀራት ከመንግስት የሰማናት አንዲትም ቃል ግን የለችም ”፡፡
ባገቱ ሰሞን ተማሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸው በስልክ እንዲገናኙ ይፈቅዱ የነበሩት አጋቾቹ አሁን ያን ካደረጉ 3 ወራትን አስቆጥረዋል፡፡
ከመጀመሪያው የታህሳስ ሳምንት ወዲህ የቤተሰቦቹን ደምጽ ለመስማት ለመገናኘትም የቻለ ተማሪም ከታጋቾቹ መካከል የለም፡፡
“በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው የግንኙነት መቋረጥ ተቀባይነት የሌለውና የህዝብን መረጃ የማግኘት እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚጻረር ነው” እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡
በመሆኑም “የታጋች ቤተሰቦች ስለልጆቻቸው በቀላሉ መረጃን እንዲያገኙ ብቻም ሳይሆን ኮሮናን የተመለከቱ ወሳኝ የህብረተሰብ ጤና መረጃዎችን ለህዝብ ለማድረስ የተቋረጠው ግንኙነት ወደ ነበረበት ሊመለስና ሊስተካከል ይገባል”፡፡
ተማሪዎቹ በዩኒቨርስቲው የተቀሰቀሰውን የብሄር ግጭት በመሸሽ በጋምቤላ በኩል ወደ ቤተሰባቸው ለመመለስ ሲሞክሩ መታገታቸው ይታወሳል፡፡
ይህም ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ በማህበራዊ የተስስር ገጾች ሳይቀር መንግስት ታጋቾቹን እንዲያስለቅቅ እና ጥፋተኞችን ለህግ እንዲያቀርብ የሚያጠይቁ ዘመቻዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
ከታጋቾቹ መካከል አንዱ ስለመሆኑ የተነገረለት ተማሪ ገብረ ስላሴ ሞላ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሁሉ በጉዞ ላይ ሳሉ ቄሮ በተሰኘው የኦሮሞ ወጣቶች ቡድን መታገታቸውንና ወደ ጫቃ መወሰዳቸውን በጊዜው ለአጎቱ አሳውቆም እንደነበር አምነስቲ ጠቁሟል፡፡
ከእገታው አምልጣ በመጣችው ተማሪ አስምራ ሹምዬ በኩል እገታውን የተመለከቱ መረጃዎች ለተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች ሲደርሱ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡