ለዩክሬን የላኩት የጦር መሳሪያ የሩሲያን ግዛት እንዲመታ የፈቀዱ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ፈረንሳይ፣ ብሪታንያና ፖላንድን ጨምሮ የዋሽንግተን አጋር ሀገራት ፕሬዝዳንት ባይደን ለኬቭ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ እየጠየቁ ነው
ፑቲን በበኩላቸው ምዕራባውያን “በእሳት ከመጫወት” እንዲቆጠቡ አሳስበዋል
አሜሪካ ምዕራባውያን ወደ ዩክሬን የላኩት የጦር መሳሪያ የሩሲያን ግዛት አልፎ ጥቃት ማድረስ እንዲችል ፈቃድ እንድትሰጥ እየተጠየቀች ነው።
በተለይ በዚህ ሳምንት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ)ን ጨምሮ የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ኬቭ ምዕራባውያን በላኩላት መሳሪያዎች የሩሲያን ግዛት መምታት እንድትችል ሊፈቀድ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዩክሬን ከሰሞኑ የምዕራባውያንን የጦር መሳሪያ በሩሲያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎችን እንድትመታባቸው ሊፈቀድላት ይገባል ማለታቸውን ፍራንስ24 አስታውሷል።
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ እስካሁን በአደባባይ በግልጽ ለኬቭ ይፈቀድላት የሚል አስተያየት ባይሰጡም “(የኬቭ) የመከላከል እርምጃ በግዛቷ ውስጥ ብቻ ላይገደብ ይችላል፤ የወራሪውን ግዛት ማጥቃትም ያካትታል” ሲሉ በተዘዋዋሪ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል ነው የተባለው።
የኔቶ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግም ምዕራባውያን ኬቭ በሩሲያ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት አድርሳ ራሷን አስቀድማ እንድትከላከል ሊፈቅዱ ይገባል ሲሉ ለዘኢኮኖሚስት ተናግረዋል።
ብሪታንያ ቀደም ብላ ወደ ዩክሬን የላከቻቸውን የጦር መሳሪያዎች በምን መልኩ ልጠቀም የሚለውን ራሷ ኬቭ ናት የምትወስነው በማለት ይሁንታዋን መስጠቷ ይታወሳል።
ፖላንድም በዚህ ሳምንት ለኬቭ ድጋፏን የሰጠች ሲሆን፥ አንዳንድ የኔቶ አባል ሀገራት ግን ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ የሩሲያን ወታደራዊ ጣቢያዎ ከመምታት ይልቅ የኬቭን የአየር መከላከያ ስርአት ማጠናከሩ ይሻላል ብለዋል።
ምዕራባውያን ለኬቭ የገቡትን ቃል በፍጥነት ካለመፈጸም ባለፈ በላኩት መሳሪያ ላይ ገደብ መጣላቸው “ፍትሃዊ” አይደለም ሲሉ የተደመጡት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ የአሜሪካን ምላሽ እየጠበቁ ነው።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ዋሽንግተን በጉዳዩ ላይ ያላት አቋም “እንደየአውደ ውጊያው ሁኔታ የሚለዋወጥ ነው” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ሩሲያ በበኩሏ አሜሪካ በአጋሮቿ በኩል እያሰማችው ማስጠንቀኢያ አዘል መልዕክትን በቀላሉ አልመለከተውም ብላለች።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ ግዛት ላይ ለሚፈጸም ጥቃት ኬቭን መሳሪያ ያስታጠቁ ሃገራት ሃላፊነት ይወስዳሉ ያሉ ሲሆን፥ በተለይ “አነስተኛ የአውሮፓ ሀገራት” በእሳት ከመጫወት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ተንታኞች ግን ዩክሬን ከዚህ ቀደምም ከምዕራባውያን የተላኩላትን የጦር መሳሪያዎች ተጠቅማ በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃት ፈጽማለች፤ የአሁኑ ለየት የሚያደርገው ሀገራቱ በግልጽ መናገራቸው ነው ይላሉ።
ሞስኮም የፓሪስ፣ ለንደን እና ዋርሳው የሰሞኑ ጥሪና የዋሽንግተን ቀጣይ ውሳኔ የዩክሬኑን ጦርነት አድማስ እንደሚያሰፋና የኒዩክሌር ጦርነት ሊጀመር እንደሚችል ማስጠንቀቋን ቀጥላለች።