በአፍሪካ ህብረት የታገዱ ሀገራት መሪዎች በብራሰልሱ የአውሮፓ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ሳይሳተፉ ቀሩ
ሱዳንን ጨምሮ ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ጊኒ የመሳሰሉ ሀገራት በጉባኤው ያልተሳተፉ ሀገራት ናቸው
ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ወደ 40 የሚጠጉ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በጉባኤው ተሳታፊ ሆነዋል
በአፍሪካ ህብረት የታገዱ ሀገራት መሪዎች በብራሰልሱ የአውሮፓ-አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ሳይሳተፉ ቀሩ፡፡
በአውሮፓ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ያልተሳተፉትና በመሪዎቻቸው ሳይወከሉ የቀሩት ሀገራትም በፖለቲካ ትኩሳት እየተናጠች የምትገኘው ሱዳንን ጨምሮ መፈንቅለ መንግስት የተካሄደባቸው ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ጊኒ መሆናቸው ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ወደ 40 የሚጠጉ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እንደተሳተፉበት የሚነገርለት የብራሰልሱ ጉባኤ በአውሮፓ-አፍሪካ የላቀ ብልጽግናን እንዴት መገንባት እንደሚቻል ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።
የመሪዎቹ ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ እና ወቅታዊውን የጤና ቀውስ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ታላቅ የአፍሪካ-አውሮፓ የኢንቨስትመንት ፓኬጅ ለመክፈት በሚያስችል አጀንዳም የሚመክር ይሆናል።
የሰላም እና የጸጥታ ጉዳይና መረጋጋትን ለማስፈን የሚረዱ መፍትሄወችን ማበጀት የሚለው ጉዳይም የመሪዎቹ ዐቢይ አጀንዳ ነው መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ “የላቀ ብልጽግና” የአፍሪካ እና የአውሮፓ መሪዎች የ2030 የጋራ ራዕይ ሆኖ በተሳታፊዎቹ የሚጸድቅ ይሆናል፡፡
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማኪ ሳል ‘’የእኛ የጋራ ምኞት አፍሪካውያን እና አውሮፓውያን ለዚህ ስብሰባ የታደሰ አጋርነት ላይ መድረስ፣ ማዘመን እና በተግባር ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ ነው’’ ማለታቸውንም ነው ዩሮ ኒውስ የዘገበው፡፡።
የአውሮፓ ህብረት ለአፍሪካ ኢንቨስትመንት 150 ቢሊየን ዩሮ መድቦ ለአረንጓዴ እና ዲጂታል ሽግግር፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ጤና እና ትምህርት እገዛ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ከተካሄደ ከአምስት ዓመት በኋላ የሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤው ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡