የመሪዎቹን ጉባዔ ተከትሎ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ
የሁለቱ ግንኙነት ለግጭቶች ምላሽ ለመስጠት እና ዴሞክራሲን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት
ብሊንከን የአሜሪካ እና የህብረቱን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል
35ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ተከትሎ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይቱ የአሜሪካ እና የህብረቱን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ደውለው መነጋገራቸውን ብሊንከን አስታውቀዋል፡፡
የሁለቱ ግንኙነት ለግጭቶች ምላሽ ለመስጠት እና ዴሞክራሲን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ያስታወቁት፡፡
በውይይቱ የሱዳን፣ የማሊ እና የቡርኪና ፋሶን ጨምሮ ስለ አፍሪካ የፖለቲካ እና ጸጥታ ይዞታ መወሳቱን ያስታወቀው ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤታቸውም ስለ አህጉሪቱ ዴሞክራሲ መጎልበት አስፈላጊነት ላይ ተወያይተዋል ብሏል፡፡
ብሊንከን ከህብረቱ ጋር ላላት ግንኙነት በተለይም የህብረቱ መሪዎች በሰሞነኛው ጉባዔያቸው ከተስማሙባቸው የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ላይ ሃገራቸው ቅድሚያ እንደምትሰጥ ደግመው ለማረጋገጥ እንደሚፈልጉ በውይይቱ አንስተዋልም ብለዋል ጽህፈፈት ቤቱ፡፡
ህብረቱ በበኩሉ ውይይቱን በተመለከተ ያሳወቀው ነገር የለም፡፡
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡