በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ እንስሳት ሞተዋል ተባለ
በድርቁ የተጎዱትን ለመደገፍ 130 ሚሊዮን ዶላር ይስፈልጋል ተብሏል
ከመጋቢት እስከ ግንቦት በአካባቢው ዝናብ ካልዘነበ ድርቁ እጅግ ከባድ ጉዳት እንደሚያደርስ ፋኦ ገልጿል
በምስራቅ አፍሪካ በተከሰተው ድርቅ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ እንስሳት ሞተዋል ተባለ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።
ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ደግሞ በድርቁ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሀገራት ሲሆኑ ከመጪው መጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ወራት ውስጥ ዝናብ ካልዘነበ የጉዳት መጠኑ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም ድርጅቱ አስታውቋል።
በነዚህ ሀገራት ያሉ የድርቅ ተጎጂዎች ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ 130 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ያለው ፋኦ በተጠቀሱት ወራት ውስጥ ዝናብ ከዘነበ አርብቶ እና አርሶ አደሮቹ ከጉዳታቸው በቀላል ድጋፎች ያገግማሉ ብሏል።
በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ መነሻው ባሳለፍነው ክረምት ወራት ውስጥ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ በመዝነቡ እና በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ ምንም ዝናብ አለመዝነቡ ቢሆንም፤ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ባሉት ወራት ውስጥ ዝናቡ አለመዝነቡ ጉዳቱን አባብሶታልም ተብሏል።
በድርቁ ምክንያትም በሶማሊያ የ58 በመቶ ምርት ሲቀንስ በኬንያ ደግሞ ድርቁ በተከሰተባቸው ደቡባዊ ምስራቅ አካባቢዎች 70 በመቶ የምርት እጥረት ማጋጠሙም ድርጅቱ በሪፖርቱ ገልጿል።
በመሆኑም ለድርቅ ተገጂዎች የእንስሳት መኖ፣ ምግብ እና ምርጥ ዘሮችን እንዲገዙ የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።
በኬንያ ብቻ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን እንስሳት በድርቁ ምክንያት የሞቱ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ 240 ሺህ የቤት እንስሳት ሞተዋል።
በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 13 ሚሊዮን ዜጎችን የጎዳ ሲሆን ከፈረንጆቹ 1988 ዓ.ም በኋላ በታሪክ አውዳሚው የድርቅ እንደሆነ ድርጅቱ ገልጿል።