ዜጎቻቸው አጫጭር የሆኑ የዓለም ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
አማካይ የዜጎች ቁመት ከፍተኛ እና ዝቅተኛ በሆነባቸው ሀገራት ህጻናት መካከል የ20 ሴንቲሜትር ቁመት ልዩነት ተመዝግቧል

የእስያ ሀገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው አጫጭር ዜጋ በማስመዝገብ ቀዳሚ ናቸው
በበለጸጉት ሀገራት የዜጎች አማካይ ቁመት እየጨመረ ሲሄድ በታዳጊ ሀገራት ደግሞ እየቀነሰ ነው ተባለ።
የለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፥ በአለማቀፍ ደረጃ ለሚታየው የቁመት ለውጥ የአየር ንብረት ለውጥ እና አመጋገብ ተጽዕኖው የጎላ ነው።
የህብረ በራሂ (ጂን) እየታየ ለሚገኘው የሰዎች ቁመተ ለውጥ ድርሻ ቢኖረውም በአለማቀፍ ደረጃ ከሚታየው ለውጥ አንጻር ትልቅ ተጽዕኖ እንደሌለውም ጥናቱን ያደረጉት ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
በጥናቱ የዜጎቻቸው አማካይ ቁመት ከፍተኛ እና ዝቅተኛ ሆኖ በተመዘገበባቸው ሀገራት የሚገኙ ህጻናት ቁመት የ20 ሴንቲሜትር ልዩነት እንዳለው ያሳያል።
እንደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና ቻይና ባሉ ሀገራት አማካይ የዜጎች ቁመት ጭማሪ ሲያሳይ በኡጋንዳ እና ሴራሊዮን ቅናሽ አሳይቷል ነው የተባለው።
አፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር በጥናቱ አማካይ የዜጎቻቸው ቁመት ዝቅተኛ ሆኖ የተመዘገበባቸውን 10 ሀገራት ይፋ አድርጓል።
1. ቲሞር ሌስቴ - 155.47 ሴንቲሜትር
በደቡብ ምስራቅ እስያ በምትገኘው ቲሞር ደሴት የዜጎች አማካይ ቁመት 155.47 ሴንቲሜትር ነው። ወንዶቹ (159.79 ሴንቲሜትር) ከሴቶቹ (151.15 ሴንቲሜትር) የተሻለ ቁመት አላቸው።
2. ላኦስ - 155.89 ሴንቲሜትር
የታይላንድ እና ቬትናም ጎረቤቷ ላኦስም አጫጭር ዜጎች ካላቸው ሀገራት ተመድባለች። በላኦስ አማካይ የሰዎች ቁመት 155.89 ሴንቲሜትር ነው።
3. ማዳጋስካር - 156.36 ሴንቲሜትር
የአለማችን አራተኛዋ ሰፊ ደሴት ማዳጋስካር ዝቅተኛ አማካይ የዜጎች ቁመት ካላቸው ሀገራት 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በአፍሪካዊቷ ሀገር አማካይ የዜጎች ቁመት 156.36 ሴንቲሜትር ነው። የወንዶች አማካይ ቁመት 161.54 ሴንቲሜትር ሲሆን የሴቶቹ 151.18 ሴንቲሜትር ነው ተብሏል።
4. ጓቲማላ - 156.39 ሴንቲሜትር
የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ጓቲማላም አጫጭር ዜጎች በብዛት ከሚገኝባቸው የአለማችን ሀገራት ተርታ ተመድባለች። በሀገሪቱ አማካይ የዜጎች ቁመት 156.39 ሴንቲሜትር ሲሆን ወንዶቹ ከሴቶቹ በ14 ሴንቲሜትር ይረዝማሉ ተብሏል።
5. ፊሊፒንስ - 156.41 ሴንቲሜትር
ከ7 ሺህ በላይ ደሴቶች ባሉባት የደቡብ ምስራቅ እስያዋ ፊሊፒንስ አማካይ የዜጎች ቁመት 156.41 ሴንቲሜትር ነው። ፊሊፒናውያን ወንዶች 163.2 ሴንቲሜትር የሚረዝሙ ሲሆን፥ የሴቶቹ አማካይ ቁመት 149.6 ሴንቲሜትር ነው ተብሏል።
6. ኔፓል - 156.58 ሴንቲሜትር
ሌላኛዋ የደቡብ ምስራቅ እስያዋ ሀገር ኔፓል ከላኦስ እና ፊሊፒንስ በመቀጠል አጫጭር ዜጎች የሚበዙባት ተብላ ተመዝግባለች። በሀገሪቱ አማካይ የዜጎች ቁመት 156.58 ሴንቲሜትር ሲሆን፥ የወንዶቹ ቁመት በአማካይ 162.31 ሴንቲሜትር ነው።
7. የመን - 156.92 ሴንቲሜትር
ባለፉት ስምንት አመታት በጦርነት ውስጥ ባለችው የመን አማካይ የዜጎች ቁመት 156.92 ሴንቲሜትር ነው። በመካከለኛው ምስራቋ ሀገር የወንዶች አማካይ ቁመት 159.88 ሴንቲሜትር መሆኑም ተገልጿል።
8. ማርሻል ደሴቶች - 157.05 ሴንቲሜትር
በፊሊፒንስ እና ሃዋይ መካከል የምትገኘው ደሴት አጫጭር ሰዎች ይበዙባቸዋል የተባሉ ሀገራትን ተቀላቅላለች። በማርሻል ደሴቶች አማካይ የዜጎች ቁመት 157.05 ሴንቲሜትር ነው።
9. ባንግላዲሽ - 157.29 ሴንቲሜትር
በባንግላዲሽ አማካይ የዜጎች ቁመት 157.29 ሴንቲሜትር ነው። የወንዶች እና ሴቶች አማካይ ቁመትም 163.8 ሴንቲሜትር እና 150.78 ሴንቲሜትር ነው ተብሏል።
10. ካምቦዲያ - 158.11 ሴንቲሜትር
የዜጎቻቸው አማካይ የቁመት መጠን ዝቅተኛ ነው ተብለው ከተዘረዘሩት 10 ቀዳሚ ሀገራት ስምንቱ በእስያ አህጉር የሚገኙ ናቸው። በካምቦዲያ አማካይ የዜጎች ቁመት 158.11 ሴንቲሜትር ነው።
ኢንዶኔዥያ፣ ማላዊ፣ ሩዋንዳ፣ ህንድ እና ቬትናም እስከ 15ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።