270 ጥንዶችን ያጋቡት ስፔናዊ ለትዳር የወንዶች ቁመት ወሳኝ ነው ይላሉ
ስፔናዊው የካቶሊክ ቄስ ፈርናንዶ ኩይቫስ ትዳር የሻቱ 540 ሰዎችን አጋብተዋል፤ እስካሁን አንድም የተፋታባቸው የለም
ፈርናንዶ ትዳር እየፈለጉ መንገዱ ለጠፋባቸው ሰዎች የዘየዱት መላ ከስፔን እስከ ላቲን አሜሪካ ዝናቸው እንዲናኝ አድርጓል
ስፔናዊው የካቶሊክ ቄስ ፈርናንዶ ኩይቫስ ትዳር ፈላጊዎችን በማገናኘት ስኬታማ ስራቸው “ቲንደር ቄስ” የሚል ቅጽል ስም ወጥቶላቸዋል።
የቫሌንሽያ ከተማ ነዋሪው ፈርናንዶ፥ 270 ጥንዶች ጎጆ እንዲቀልሱ ማድረግ ችለዋል።
ትዳር ፈላጊ ወጣቶችን የማገናኘት ተገባራቸውን ከ14 አመታት በፊት ነው በድንገት የጀመሩት።
ሳልቫ የተባለ ወጣት ለሃይማኖታዊ ትምህርት ወደ ቄስ ፈርናንዶ ሲያመራ እምነታቸውን ያጠበቁ ቆነጃጂት ሴቶችን ይመለከታል፤ ምናልባትም አንዷ ውሃ አጣጬ ትሆናለች ብሎም መምህሩን እንዲያስተዋውቁት ይጠይቃል፤ ቀልቡ ይበልጥ ያረፈባትንም ጊለስ የተባለች ወጣት ወዲያውኑ ይተዋወቃል፤ ከአምስት ወራት በኋላም ትውውቁ ወደ ትዳር አደገ።
የሳልቫ እና ጊለስ ትዳር ለፈርናንዶ ትዳር ፈላጊዎችን የማገናኘት ተግባር ፈር ቀዳጅ ተደርጎ ይወሰዳል።
“በርካታ ሰዎች የትዳር አጋራ ፍለጋ መንገዱ ሲጠፋባቸው ይስተዋላል፤ የሃይማኖት አባቶችንም በዚህ ጉዳይ ለማማከር የሚደፍሩት ጥቂቶች ናቸው” የሚሉት ፈርናንዶ፥ ከነሳልቫ የተሳካ ጥምረት ስለትዳር ለሚያማክሯቸው ሰዎች መጠይቆችን ማስሞላት ጀመሩ።
ስም፣ እድሜ፣ ቁመት፣ የትምህርት ደረጃ፣ የስራ አይነት፣ የመኖሪያ አድራሻ፣ አጉል ባህሪያትና ልማዶችን ጨምሮ ዝርዝር ጉዳዮችን በማስሞላትም የሚስማማቸውን የትዳር አጋር ማፈላለግ ተያያዙት።
ከተጠቀሱት ዝርዝር ነጥቦች ሁሉ ግን ሁለት ጉዳዮች የትዳር ፈላጊዎቹን ለማቀራረብ ወሳኝ መሆናቸውን ያነሳሉ ፈርናንዶ፤ የወንዶች ከሴቶች ይልቅ ቁመታቸው መብለጥ እና የመኖሪያ አድራሻ አለመራራቅ።
ትዳር ፈላጊዎቹ በብዙ ነገር የሚጣጣሙ ቢመስሉም የመኖሪያ አድራሻቸው ከተራራቀ ትዳር የመመስርቱ ጉዳይ የሚሳካ አይደለም ባይ ናቸው።
በትዳር ፈላጊዎቹ የተሞሉትን ዝርዝር ባህሪያት እያጤኑ ጥሩ ጥንዶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ላመኑባቸው የእጩ ተጋቢዎቹን ዝርዝር ባህሪያት የተሞላበት ፎርም እና ምስላቸውን ጨምረው ይልካሉ(የሴቷን ለወንዱ፤ የወንዱን ለሴቷ)። ሁለቱም ከተስማሙም ስልክ ቁጥራቸውን እንዲለዋወጡ በማድረግ የትዳር ጉዞው ይጀመራል።
ይህ ተግባራቸው ታዲያ ላለፉት 14 አመታት 270 ጥንዶችን በትዳር ሲያጣምር አንድም ፍቺ አለማስተናገዱ ዝናቸውን ከስፔን ተሻግሮ እስከ ላቲን አሜሪካ ሀገራት አዝልቆታል።
በየቀኑ ከ20 በላይ የትዳር አጋር ፈልጉልኝ ጥያቄ በኦንላይን የሚደርሳቸው “ቲንደር ቄስ” ፈርናንዶ፥ በምችለው አቅም ምላሽ እየሰጠኋቸው ነው ይላሉ፤ ነገር ግን ከትውውቅ በኋላ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደሌላቸው ያክላሉ።
ትዳር እየፈለጉ መንገዱ የጠፋባቸውን በማስተዋወቅ ላይ የሚገኙት ስፔናዊው ፈርናንዶ ኩይቫስ፥ ትዳር ፈላጊዎቹ ጥንዶች እምነታቸውን ያጠበቁ መሆናቸው ስራቸውን ስኬታማ እንዳደረገው መናገራቸውንም ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።