በዓለም የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር አዳዲስ ሪከርዶች እየተመዘገቡ ነው
በመላው ዓለም ከ134 ሚሊዬን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን የ2.9 ሚሊዬን ሰዎች ህይወት አልፏል
ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 131,968 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በተረጋገጠባት ህንድ አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ13 ሚሊዬን አሻቅቧል
በተለያዩ የዓለም ሃገራት ያለው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ፤ አዳዲስ የቁጥር መረጃዎችም እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በሚገኝባት ኢትዮጵያ ተጨማሪ 2 ሺ 121 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
ይህ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገው 7 ሺ 757 የላቦራቶሪ ናሙናዎች ምርመራ የተለየ ነው፡፡ ከናሙናዎቹ 27 በመቶና ከዚያ በላይ የሚሆኑት በቫይረሱ መያዛቸውን ያመለክታል፡፡
አሁን ባለው ወቅታዊ የቫይረሱ የስርጭት ሁኔታ በኢትዮጵያ ከ4 ሰዎች አንዱ በቫይረሱ ሳይያዝ እንዳልቀረ ይገመታል፡፡
የ20 ሰዎች ህይወትም አልፏል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ በቫይረሱ ተይዘው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 53 ሺ 833 ሲሆን የ3 ሺ 78 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
ባላት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ብዛት በሁለተኛነት የምትጠቀሰው ህንድም ከባለፈው ከወርሃ ጥቅምት አጋማሽ ወዲህ ከፍተኛ ነው የተባለ እለታዊ የቫይረሱን ተጠቂዎች ቁጥር አስመዝግባለች፡፡
ህንድ ከአሜሪካና ብራዚል ቀጥሎ በከፍተኛ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ትጠቀሳለች፡፡
ባለፉት 24 ሰዓታትም 131,968 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ 780 ሰዎች ሞተዋል፡፡
ይህም አጠቃላይ በሃገሪቱ ያሉትን የቫይረሱን ተጠቂዎች ቁጥር 13.06 ሚሊዬን የሚያደርስ ነው፡፡
1 ሚሊዬን ያህሉ ባለፉት 11 ቀናት የተያዙ መሆናቸውንም ነው የሲኤን ኤን ዘገባ የሚያመለክተው፡፡
በብራዚል 13.28 ሚሊዬን ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡
ባሳለፍነው ማክሰኞ በብራዚል የ4,195 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ ይህም ከፍተኛ ነው በሚል በሪከርድነት መመዝገቡ የሚታወስ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ፕሬዝዳንት ጃኤር ቦልሶናሮ እና መንግስታቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አያያዝ ላይ ምርመራ እንዲደረግ የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዟል መባሉም ይታወሳል፡፡
አሜሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች፡፡ ከ31 ሚሊዬን በላይ ሰዎችም በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ የ560,115 ሰዎች ህይወትም አልፏል፡፡
በመላው ዓለም 134,035,138 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የሚያመለክተው የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ የ2,904,504 ሰዎች ህይወት ማለፉንም ይጠቁማል፡፡