ኢትዮጵያ በቀጣይ 2 ወራት ውስጥ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዶዝ የኮሮና ክትባት እንደምታገኝ ተገለጸ
ክትባቱ መሰጠት የተጀመረው መጋቢት 4፣2013 ዓ.ም ነበር
ኢትዮጵያ በቀጣይ አንድ አመት ውስጥ የተጋላጭነታቸው መጠን እየታየ 20 ሚሊዮን ዜጎች ይከተባሉ ተብሏል
ኢትዮጵያ ኮቫክስ በተሰኘው የክትባት አስተባባሪ ቡድን አማካኝነት 2.2 ሚሊዮን ዶዝ ከአንድ ወር በፊት መቀበሏ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከመጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የአስትራ ዜኒካ ክትባት በአገር አቀፍ ደረጃ የመስጠት መርሐ ግብርን በይፋ ጀምራለች።
ለቀጣዩ አንድ ዓመት ውስጥም ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ክትባቱ እንደተጋላጭነታቸው መጠን መሰጠቱ እንደሚቀጥል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ክትባቱን በቅድሚያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በስራ ላይ ላሉ ለጤና ባለሙያዎች በመስጠት ላይ ሲሆን ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ ደግሞ እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ እና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ዜጎች ከትባቱን በመውሰድ ላይ ናቸው።
አል ዐይን አማርኛ በክትባቱ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን አናግሯል።
በሚኒስቴሩ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ብሔራዊ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሙሉቀን ዮሀንስ እንዳሉት በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ከትባቶችን እንድታገኝ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እና ከሌሎች የፌደራል እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ 5.4 ሚሊዮን ዶዝ የኮሮና ቫይረስ ክትባት በኮቫክስ በኩል እንደምታገኝም ዶክተር ሙሉቀን ዮሀንስ ተናግረዋል።
ከአስተራ ዘኒካ ክትባት በተጨማሪ ሌሎች የክትባት አይነቶችን ለማግኘት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም አስተባባሪው ገልጸዋል።
አሁን ላይ ክትባቱን እያገኙ ካሉ የጤና ባለሙያዎች እና እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ እንዲሁም ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ዜጎች በተጨማሪ በቀጣይ ለተጋላጭ የህብረተሰብ ከፍሎች ክትባቱ ይሰጣል ተብሏል።
በቀጣይ በተለይም ከብዙ የህብረተሰብ ጋር ቀጥታ ንኪኪ ያላቸው አገለግሎት ሰጪ ተቋማት ሰራተኞች ከትባቱን እንደሚወስዱ ዶክተር ዮሀንስ ተናግረዋል።
በተለይም የባንክ ቤት ሰራተኞች፤መምህራን፤በከተሞች ያሉ የጸጥታ ሀይል እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ሰራተኞች ክትባቱ እንደሚሰጣቸው አማካሪው ገልጸዋል፤
እስካሁን ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች ላይ ከተለመዱት ምልክቶች ውጪ ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን የገለጹት ዶክተር ዮሀንስ እስካሁን ክትባቱ በተሰጠበት ላይ መቅላት፤ራስ ምታት፤መዛል እና እብጠት ውጪ የጋጠመ ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ክትባቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመሰጠት ላይ ሲሆን የጸጥታ ችግር ከሌለባቸው አካባቢዎች ውጪ በሁሉም ስፍራዎች ክትባቱ በተቀመጠው አሰራር መሰረት እየተሰጠ እንደሆነም ተገልጿል።
በተወሰኑ አካባቢዎች ክትባቱን ላልተገባ አካል የመስጠት ችግር እንዳለ ሀሳብ እየተነሳ ነው በሚል ለዶክተር ዮሀንስ ላነሳንላቸው ጥያቄም ክትባቱን መስጠት ከመጀመሩ በፊት የሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች አመራሮች በተገኙበት ግልጽ አሰራር ዘርግተናል፤ ከተቀመጠው አሰራር ውጪ ክትባቱን ለማይገባው ሰው የሰጠ አካል ካለ በህግ ይጠየቃል እስካሁን ችግሩ እንዳለ በግልጽ የቀረበ ነገር የለም ሲሉ መልሰውልናል።