ሪፖርት የሚደረጉ ኬዞች ቁጥር በ15 በመቶ መቀነሱ ተሰምቷል
በመላው ዓለም ያለው የኮሮና ቫይረስ የስርጭት መጠን እየቀነሰ ነው ተባለ፡፡
አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ ኦሚክሮን ሪፖርት ከተደረገበት ከባለፉት ሶስት ወራት ወዲህ ሳምንታዊ የሞት ምጣኔው በ16 በመቶ ሪፖርት የሚደረጉ ኬዞች ቁጥር ደግሞ በ15 በመቶ መቀነሱ ተሰምቷል፡፡
ሆኖም በእስያ የስርጭት ምጣኔው እምብዛም ቅናሽ አላሳየም፡፡ ይልቁንም የ4 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል፡፡ የሞት ምጣኔው በ0.9 ብቻ ነው ዝቅ ያለው፡፡ ደቡብ ኮሪያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቬትናምና ሆንኮንግ አዳዲስ ዕለታዊ የተጠቂዎች ቁጥር ሪከርዶችን እያስመዘገቡ ነው፡፡
እስከ ቅርብ ወራት ድረስ ከ100 ያላለፉ እለታዊ ኬዞችን ሪፖርት ስታደርግ በነበረችው ሆንግ ኮንግ በባለፉት ተከታታ ቀናት 17,053 እና 26,026 ኬዞችን ሪፖርት አድርጋለች፡፡
ኒውዝላንድም ወረርሽኙ ዳግም እያገረሸ ካስቸገራቸው ሃገራት መካከል ነች፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ 224 ሃገራትን እና ግዛቶችን አዳርሷል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በጠቅላላ 436 ሚሊዮን 122 ሺ 374 ሰዎች ያጠቃ ሲሆን የ6 ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡
በኢትዮጰያም በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀላል የማይባል ቅናሽ እያሳየ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ 4,200 የላቦራቶሪ ናሙና ምርመራ 49 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል። በአጠቃላይ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 468,674 ደርሷል። በሌላ በኩል 61 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ 416,704 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።