በትሪሊዮን ከሚቆጠረው የአሜሪካ የኮሮና ማገገሚያ በጀት ውስጥ በትንሹ መቶ ቢሊዮን ዶላር ተሰርቋል ተባለ
ዋሽንግተን ማገገሚያ ነው በሚል 3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር መመደቧ ይታወሳል
በስራ አጥ ስም 87 ቢሊዮን ዶላር ያህል ሳይባክን አልቀረም ተብሏል
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቋቋም በሚል ከበጀተው በትሪሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ውስጥ በትንሹ መቶ ቢሊዮን ዶላር ተሰርቋል ተባለ፡፡
በጀቱ በወረርሽኙ ምክንያት የደቀቀውን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት በሚል አነስተኛዎቹን ጨምሮ የተለያዩ የቢዝነስ አንቀሳቃሾችን እንዲሁም ስራ ያጡ አሜሪካውያንን ለመደጎም የተበጀተ ነበር፡፡
ሆኖም በቢሊዮን ከሚቆጠረው በጀት ቢያንስ መቶ ቢሊዮን ዶላር ያህሉ በተለያዩ መንገዶች መሰረቁን የራሷ የአሜሪካ የደህንነት ምንጮች አሳውቀዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 87 ቢሊዮን ዶላር ያህሉ በስራ አጥ ስም ሳይመዘበር አልቀረም ተብሏል፡፡
ምንጮቹ ከሃገሪቱ ሰራተኛ እና አነስተኛ ቢዝነስ አስተዳደር ቢሮዎች የተገኙ መረጃዎችን በመተንተን ነው ገንዘቡ መሰረቁን የተመለከተ መረጃ ያወጡት፡፡
መረጃው ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ተፈጽመው በዐቃቤ ህግ እየታዩ ያሉ የስርቆትና ማጭበርበር ወንጀሎችን አያካትትም እንደ ምንጮቹ ገለጻ፡፡
በእርግጥ እስካሁን ለማገገሚያ ይሆን ዘንድ ከተበጀተው 3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ውስጥ ሶስት በመቶ ያህሉ ብቻ ነው የተሰራጨው፡፡ ከዚህም ውስጥ ነው በትንሹ መቶ ቢሊዮን ዶላር ተሰርቋል የተባለው፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ባደረጉት ምርመራ የተጭበረበረ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ መያዛቸውንና በተመሳሳይ መንገድ በግብይት መልክ ለመጭበርበር የተዘጋጀን ከ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር ማስመለሳቸውን ስርቆቱን ያጋለጡ የደህንነት ተቋማት አስታውቀዋል።
ከዚሁ ጋር የተያያዙ ከ900 በላይ ጉዳዮችን እየመረመሩ እንደሆነ እና እስካሁን 100 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል፡፡