መንግሥት ጋዜጠኛ በላይ ማናዬን ከእስር እንዲለቅ ሲፒጂ ጠየቀ
የኢትዮ ኒውስ መስራች እና ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከታሰረ 22 ቀን ሆኖታል
ጋዜጠኛው በአማራ ክልል ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በሚሰራቸው ዘገባዎች ምክንያት ታስሯል ተብሏል
መንግሥት ጋዜጠኛ በላይ ማናዬን ከእስር እንዲለቅ ሲፒጂ ጠየቀ።
የኢትዮ ኒውስ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ህዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም የጸጥታ ክልሎች አራት ኪሎ በሚገኘው ቢሮው አካባቢ እንዳሰሩት የስራ ባልደረባው እና ባለቤቱ ተናግረዋል።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲፒጂ ባወጣው ሪፖርት ጋዜጠኛ በላይ ከታሰረ ሶስት ሳምንት እንዳለፈው እና እስካሁን ፍርድ ቤትም እንዳልቀረበ አስታውቋል።
የሲፒጂ ሰብሰሀራ አፍሪካ ተወካይ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ እንዳሉት በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የመስራት ነጻነታቸው መጎዳቱን ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኛ በላይ ማናዬን በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቅ ሲፒጂ አሳስቧል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት የጋዜጠኞችን እስር እንዲያቆምም ሲፒጂ በድረገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ ጥሪ አቅርቧል።
የጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ባለቤት በላይነሽ ንጋቱ ባለቤቷ አንድ ጊዜ ከታሰረበት ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሄዳ እንደጠየቀችው የተናገረች ሲሆን በአማራ ክልል ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር አያይዘው እንዳሰሩት ነግሮኛል ማለቷ ተገልጿል።
ኢትዮ ኒውስ የተሰኘው ይህ የዩቲዩብ ሚዲያ በአማራ ክልል ያሉ ሁኔታዎችን በስፋት ከሚዘግቡ ሚዲያዎች መካከል ዋነኛው ሲሆን የጋዜጠኛ በላይ ማናዬ እስርም ከዚህ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።
የፌደራል መንግሥት "የክልል ልዩ ሀይሎችን ዳግም ማደራጀት" በሚል የአማራ ክልል ልዩ ሀይልን ካፈረሰበት ካሳለፍነው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በክልሉ ጦርነት ተቀስቅሷል።
በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ይህ ጦርነት መስፋፋቱን ተከትሎ የክልሉ ሁኔታ ከአቅሜ በላይ ነው ማለቱን ተከትሎም ካሳለፍነው ሀምሌ ወር ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተደንግጓል።
አሁን ላይ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ መሆኑን መንግሥት ቢገልጽም በበርካታ ቦታዎች ላይ ጦርነት እየተካሄደ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችም በመስተጓጎል ላይ ናቸው።