ክርስቲያኖ ሮናልዶ 700 ጨዋታዎችን በማሸነፍ የመጀመሪያው የእግር ኳስ ተጫዋች ሆነ
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ለአምስት የእግር ኳስ ክለቦች በተጫወተባቸው ጊዜዎች 700 ድሎችን በመቀዳጀት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል
ወጣቱ ትውልድ ሮናልዶ እያስመዘገባቸው የሚገኙ ክብረወሰኖችን ለማሻሻል ብዙ ጊዜ ሊወስድበት እንደሚችል የስፖርት ጋዜጠኖች እየጻፉ ነው
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሳኡዲ ሊግ አዲስ ክብረወሰንን በማስመዝገብ ሌላ ታሪካዊ ድል መጻፍ ችሏል፡፡
ሮናልዶ በአጠቃላይ የእግር ኳስ ህይወቱ 700 ጨዋታዎችን በማሸነፍ በታሪክ የመጀመሪያው እና ብቸኛው እግር ኳስ ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡
አልናስር አል ርድን 2-1 በሆነ ውጤት ባሸነፈበት ጨዋታ አንድ ግብ ያቆጠረው ሮናልዶ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር የቡድን አጋሮቹ ኳስ እንዲሰጡት በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ተስተውሏል፡፡
ፖርቹጋላዊው ኮከብ የልጅነት ብቃቱን ካዳበረበት ስፖርቲንግ ሊዝበን ጀምሮ አሁን እስከሚገኝበት የሳኡዲው አልናስር ድረስ ለአምስት ክለቦች ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡
- “ሪከርዶች ያሳድዱኛል” ያለው ክርስቲያኖ ሮናልዶ እስካሁን ምን ያክል በእጁ አስገብቷል?
- ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳስ ታሪክ 900 ግቦችን በማስቆጠር የመጀመርያው ሰው ሆነ
በስፖርቲንግ ሊዝበን 13 ጨዋታዎች፣ በሪያልማድሪድ 316፣ በማንችስተር ዩናይትድ 91፣ በጁቬንቱስ 66 እንዲሁም በአልናስር 66 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል፡፡
በቅርቡ በሁሉም ውድድሮች 900 እና ከዛ በላይ ግቦችን በማስቆጠር በታሪክ የመጀመሪያው ተጫዋች የሆነው በርካታ ሪከርዶችን የሰባበረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ አሁንም አስገራሚ ክብረወሰኖችን እያስመዘገበ ቀጥሏል፡፡
ስፖርት ቶክ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እያስመዘገባቸው የሚገኙ ክብረወሰኖች ያለጥርጥር ከክፍለዘመኑ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል የሚያስመድበው ነው ብሏል፡፡
ተጫዋቹ ከፍ አድርጎ ያስቀመጣቸው ክብረ ወሰኖች በተቀናቃኞቹ እና በወጣቱ ትውልድ ለመቀለብስ አደጋች እንደሆኑም ተነግሯል፡፡
ከከርስቲያኖ የዋንጫ ማደርደሪያ ሳጥን ላይ የሚጎድለው የአለም ዋንጫ ነው፤ ሮናልዶ በ2026 የአለም ዋንጫ በሚዘጋጅበት ጊዜ እድሜው 41 አመት ይሞላዋል፡፡
ከሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአለም ዋንጫን ማንሳት የሁልጊዜ ምኞቱ እንደሆነ የሚናገረው ሮናልዶ በቀጣዩ አመት በሚከናወነው አለምአቀፋዊ ውድድር ላይ በሚኖረው ተሳትፎ ዙሪያ እርግጠኛ የሆነ መረጃ አልወጣም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ ውድድሮች ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ባደረጋቸው ውድድሮች በ217 ጨዋታዎች 135 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
በክለቦች የሚኖረው የእግር ኳስ ህይወት በሳኡዲ አረብያው አልናስር ሊጠናቀቅ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠው ሮናልዶ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ አንድ ሺህ ከፍ ማድረግ እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡
አልሂላል እና አል ኢትሀድ በጋራ እየመሩት በሚገኝው የሳኡዲ ሊግ ከመሪዎቹ በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሚገኝው አልናስር ሮናልዶ በአጠቃላይ በተሰለፈባቸው 94 ጨዋታዎች 85 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡