ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማህበራዊ ትስስር ገጾች አንድ ቢሊየን ተከታዮች በማፍራት የመጀመሪያው ሰው ሆነ
“ክብረወሰኖች ያሳድዱኛል” የሚለው ሮናልዶ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተከታይ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል
ሮናልዶ ደስታውን ባጋራበት ጽሁፍ በውድቀት እና ከፍታየ አብረውኝ ነበሩ ያላቸውን አድናቂዎቹን አመስግኗል
ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሁሉም ማህበራዊ ትስስር ገጾች ያሉት ተከታዮች ቁጥር አንድ ቢሊዮን መሻገሩን ተከትሎ አዲስ ታክ አስመዝግቧል።
“ክብረወሰኖች ያሳድዱኛል” የሚለውና የተለያዩ ክብረወሰኖችን በመሰባባር በተደጋጋሚ ስሙ የሚነሳው ሮናልዶ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተከታይ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ችሏል።
በቅርቡ በከፈተው የዩትዩብ ገጽ ከሶስት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 60 ሚሊየን ተከታዮችን አፍርቷል።
በእግር ኳስ ህይወቱ ከ900 በላይ ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን የቻለው ሮናልዶ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጥሏል።
ተጫዋቹ በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ “አንድ ቢሊዮን ተከታይ በመድረስ ታሪክ ሰርተናል ይህ ከቁጥርም በላይ ነው ለእግር ኳስ እና ከዛ ውጭ ላሉ ነገሮች ያለነን የጋራ ፍቅር ማሳያ ነው፡፡ በውደቀት እና በከፍታየ ላይ አብራችሁኝ ለነበራችሁ አድናቂዎች ክብሩን ውሰዱ” ሲል ተከታዮቹን አመስግኗል።
በማችስተር ዩናይትድ እና ሪያል ማድሪድ ደማቅ ታሪኮችን ማስመዝገብ የቻለው የእግር ኳስ ኮከብ በአሁኑ ወቅት በኢንስታግራም 639 ሚሊየን፣ በፌስቡክ 170 ሚሊየን፣ በኤክስ 113 ሚሊየን እና በዩትዩብ 60 ሚሊየን ተከታዮች አሉት።
ፎርብስ በቅርቡ ባወጣው መረጃ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ባለው ተጽእኖ ከእግር ኳስ ሜዳ ውጭ 60 ሚሊየን ዶላር ገቢ በማግኝት ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈለው ስፖርተኛ እንደሆነ አስታውቋል።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በእግርኳስ ሜዳ ሪከርዶችን የሰባበረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማህበራዊ ሚዲያዎች የአለማችን ቀዳሚው ታዋቂ ሰው ነው።
ከ600 ሚሊየን በላይ ተከታይ ባፈራበት የሜታው ኢንስታግራም ሊዮኔል ሜሲ 504 ፣ ሰሊና ጎሜዝ 424 ፣ ካይሊ ጄነር 397 ፣ ድዋይን ዘ ሮክ ጆንሰን 395 ሚሊየን ተከታዮችን በመያዝ በደረጃው ሮናልዶን ይከተላሉ።