በአንድ ሆቴል ውስጥ 6 ሰዎች በሳይናይድ ተመርዘው ሞቱ
በታይላንድ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ በመመረዝ የተጠረጠረውን ጨምሮ ስድስት ሰዎች በሳይናይድ ተመርዘው ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል
ፖሊስ እንዳለው የአስከሬን ምርመራ ውጤቱ በቀጣይ ሁለት ቀናት ውስጥ ይፋ ይሆናል
በአንድ ሆቴል ውስጥ 6 ሰዎች በሳይናይድ ተመርዘው ሞቱ።
በታይላንድ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ በመመረዝ የተጠረጠረውን ጨምሮ ስድስት ሰዎች በሳይናይድ ተመርዘው ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
የታይላንድ ፖሊስ ሳይናይድ በተባለው ኬሚካል ተበክለው ሳይሞቱ አይቀሩም ያላቸውን የስድስት ሰዎች አስከሬን በቅንጡ የባንኮክ ሆቴል ውስጥ ማግኘቱን በዛሬው እለት አስታውቋል።
ግራንድ ሃያት ኢርዋን በተባለው ቅንጡ ሆቴል ውስጥ አደገኛ የሆነው ይህ ከሚካል በመጠጫ ብርጭቆ እና በሻይ ማንቆርቆሪያ ውስጥ መገኘቱን እና ከሟቾቹ ቤተሰቦች ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ ከብድር ጋር በተገናኘ ጸብ እንደነበረ ማሳየቱን ፖሊስ ገልጿል።
ማክሰኞ ምሽት ሞተው ተገኝተዋል የተባሉት ስድስቱም ትውልዳቸው ቬትናም ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ናቸው።
የአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ(ኤፍቢአይ) ምርመራውን እያገዘ መሆኑን ፖሊስ አክሎ ገልጿል።
"በሻይ መጠጫዎች ላይ ሳይናይድ አግኝተናል፤በስድስቱም ብርጭቆዎች ላይ ሳይናይድ ተገኝቷል" ብለዋል የታይ ፖሊስ ምርመራ አዛዥ ትሪሮንግ ፒውፓን።
ፖሊስ "የሆቴሉ ሰራተኞች የሻይ ብርጭቆ፣ ሁለት የሞቀ ውሃ የያዙ ጠርሙሶች ወተት እና የሻይ ማንቆርቆሪያ አቀረቡ... ከስድስት አንዱ ሳይናይድ ቀላቀለ" ብሏል።
ፖሊስ እንዳለው የአስከሬን ምርመራ ውጤቱ በቀጣይ ሁለት ቀናት ውስጥ ይፋ ይሆናል። የቬትናም መንግስት በታይላንድ ያለው ኢምባሲው በጉዳዩ ላይ ከታይ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ሲገልጽ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደግሞ ሁኔታውን እየተከታተለው መሆኑን እና ኃላፊነት ወስደው ምርመራ የሚያካሄዱት የሀገሪቱ ባለስልጣናት ናቸው ብሏል።
በታይላንድ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ በሆነው ቦታ የተፈጠረው ይህ ክስተት ኢኮኖሚያዊ በቱሪዝም ላይ ለተመሰረተው ታይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ታይላንድ በዘንድሮው አመት ባለፈው አመት ከነበረው በ28 ሚሊዮን የጎብኝዎች ቁጥር ወደ 35 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ትጠብቃለች።
ሳይናይድ ምንድን ነው?
ሳይናይድ የሰውነት ኦክስጅን የመጠቀም አቅም የሚያስተጓጉል አደገኛ ኬሚካል ነው።
ሳይናይድ እንደ ሃይድሮጅን ሳይናይድ (ኤችሲኤን) ወይም ሳይኖጂን ክሎራይድ (CNCl) ቀለም የለሽ ጋዝ ወይም ፈሳሽ ሊሆን ይችላል። ይህ ኬሚካል በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የኬሚካል የጦር መሳሪያ ሆኖ ጥቅም ላይ መዋሉ ይነገራል።