23 ባሎችን ያገቡት አሜሪካዊቷ ሊንዳ ወልፍ የአለም ክብረወሰንን መያዛቸው ይታወሳል
በታይላንድ “ትዳር የማይጸናለት” የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው አዛውንት 14ኛ ሚስታቸውን አግብተዋል።
ሳናን ሶንግኮን የተባሉት የ69 አመት አዛውንት የፍቅረኞች ቀን በትናንትናው እለት ሲከበር ለ56 አመቷ ሶምኒዩክ ሳንግኬው ቀለበት አስረዋል።
ሳናን እና ሶምኒዩክ ከሌሎች 11 ጥንዶች ጋር በመሆን ነው ጋብቻቸውን የፈጸሙት።
ያለፉት 13 ጋብቻዎች በፍቺ የተጠናቀቁባቸው ሳናን በካራቢ ግዛት በተካሄደው ባህላዊ የጋብቻ ስነስርአት ተሞሽረዋል።
“ሶምኒዩክ የመጨረሻ ሚስቴ ትሆናለች፤ እዚህ የተገኘሁት የጋብቻ ማረጋገጫ ሰነድ ለመውሰድ ነው” ያሉት አዛውንቱ፥ በልደታቸው ቀን ጋብቻ መፈጸማቸውን የመልካም እድል ምልክት አድርገውታል።
ታይላንዳውያኑ ጥንዶች በትናንትናው እለት ቀለበት አስረው በጋብቻ ይተሳሰሩ እንጂ ላለፉት 10 አመታት አብረው መኖራቸው ተገልጿል።
“ላለፉት 10 አመታት በጋራ ስንኖር ችግር ስላላየሁባት ላገባት ወስኛለሁ” ያሉት ሳናን፥ በርካታ ሚስቶችን በማግባት ስማቸው ከፊት ከሚጠቀሱ ግለሰቦች ተርታ ተመድበዋል።
ሁለት ሚስታቸውን ቀልተው የገደሉት የእንግሊዙ ንጉስ ሄነሪ ስምንተኛ ከስድስት በላይ ሚስቶችን ማግባታቸው ይታወሳል።
በርካታ ባሎችን በማግባት በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስሟን ያሰፈረችው አሜሪካዊቷ ሊንዳ ወልፍ ስትሆን፥ 23 ጊዜ ጋብቻ መፈጸሟን የሬውተርስ ዘገባ ያወሳል።
14ኛ ሚስታቸውን ያገቡት ታይላንዳዊው ሳናን ሶንግኮን የሊንዳ ወልፍን ክብረወሰን የመስበር ፍላጎት እንዳላቸው ተጠይቀው፥ “ክብረወሰኑን መስበር አልፈልግም፤ የመጨረሻ ጋብቻዬ ነው” ብለዋል።