ታይላንድ በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ ነዋሪዎቿ ከቤት እንዳይወጡ አስጠነቀቀች
ታይላንድ በደርዘን በሚቆጠሩ ግዛቶች ከፍተኛ የሙቀት ማስጠንቀቂያ አወጣች
ተመራማሪዎች ሙቀቱን ከፍተኛ የአየር ሁኔታ ተብሎ የሚጠራ ክስተት ነው ብለዋል
የታይላንድ ባለስልጣናት ቅዳሜ ዕለት ዋና ከተማዋን ባንኮክን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ከቤት እንዳይወጡ አስጠንቅቀዋል።
አንዳንድ የእስያ ክፍሎች በዚህ ወር ከፍተኛ ሙቀት እያስመዘገቡ ሲሆን፤ በአንዳንድ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን እየታየ ነው ተብሏል።
በባንግላዲሽ እና በህንድ አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ሙቀት የኃይል ፍላጎት እንዲጨምር ያደረገ ሲሆን ይህም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የኃይል መቆራረጥ እና እጥረት አስከትሏል ነው የተባለው።
በባንኮክ የሙቀት መጠኑ 42 ዲግሪ ሴልሺየስ (100 ፋራናይት) ደርሷል።
ባለስልጣናት ነዋሪዎቹ ከቤት ውጭ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠቡ እና ከሙቀት መጨመር አደጋ እንዲጠነቀቁ አስጠንቅቀዋል።
የታይላንድ የአደጋ መከላከል እና ቅነሳ ክፍል ቢያንስ በ28 ግዛቶች የሙቀት መጠኑ ከ40 ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆን ገልጿል።
ከፍተኛው ሙቀት የኤሌክትሪክ ፍጆታ ከፍ እንዲልም አስገድዷል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ሀገሪቱ ሚያዝያ ስድስት ከ39 ሽህ ሜጋ ዋት በላይ ፍጆታ ስትወስድ፤ ባለፈው ዓመት በሚያዝያ ወር ከተመዘገበው 32 ሽህ ሜጋ ዋት በላይ መመዝገቡን የመንግስት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ተመራማሪዎች "በአሁኑ ወቅት እየሆነ ያለው በአየር ንብረት ለውጥ፣ ያልተለመደና ተጽእኖ የሚያሳድር ከፍተኛ የአየር ሁኔታ ተብሎ የሚጠራ ክስተት ነው" ብለዋል።