አልቡርሃን ንጹሃንን በጄት እየደበደበ ነው - ሄሜቲ
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በሱዳን ጦር የሚፈጸሙ ኢላማቸው ንጹሃን ላይ የሆኑ ጥቃቶችን ለመቀልበስ ጥቃት መፈጸሙንም ነው ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ የገለጹት
የሱዳን ጦርና የአርኤስኤፍ ውጊያ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል መሪው ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) አለማቀፉ ማህብረሰብ ጀነራል አልቡርሃን እየፈጸሙት ካለው የጦር ወንጀል እንዲያስቆማቸው ጠይቀዋል።
የሱዳን ጦር በሚወስዳቸው እርምጃዎች ንጹሃን ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
የአልቡርሃን ጦር በጄቶች እየፈጸማቸው በሚገኙ ኢላማቸውን የሳቱ ጥቃቶች ንጹሃን ሰለባ መሆናቸውን ያነሱት ሄሜቲ፥ አልብቡርሃን ለዚህ የጦር ወንጀል ድርጊታቸው ተጠያቂ እንደሚሆኑ መናገራቸውን የአርኤስኤ ቃልአቀባይ ጠቁመዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ከባድ የንጹሃን እልቂት ሊያደርሱ የሚችሉ የአየር ጥቃቶችን ለመቀልበስ እርምጃ መውሰዱንም አንስተዋል።
አርኤስኤፍ በትናንትናው እለት የሱዳን ጦር ተዋጊ ጄትን መቶ መጣሉን መግለጹ የሚታወስ ነው።
በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።
እስካሁንም በግጭቱ ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ንጹሃን ቁጥር 97 መድረሱ ነው የተገለጸው።
የሱዳን ዶከተሮች ኮሚቴ በጦርነቱ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አስታውቋል።
ከ365 በላይ ሰዎች የቆሰሉበት ግጭት በንግግር እንዲቆም ሀገራት ጥሪያቸውን ማስተላለፋቸውን ቀጥለዋል።
የአፍሪካ ህብረት እና የአረብ ሊግ ሁለቱን ወገኖች ለማነጋገር ጥረት ማድረግ መጀመራቸው የተነገረ ሲሆን፥ የጂቡቲ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎችም ወደ ካርቱም እንደሚያመሩ ተገልጿል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በድጋሚ ጠይቀዋል።
ሚኒስትሩ የቡድን 7 አባል ሀገራት ስብሰባ በጃፓን መካሄድ ሲጀምር ነው ጥሪውን ያቀረቡት።
“ሱዳናውያን ወታደሮች ወደ ምሽጋቸው እንዲመለሱ ይፈልጋሉ” ያሉት ብሊንከን፥ ሱዳን ህዝብ ወደሚፈልገው የሲቪል አስተዳደር እንድትመለስም ጠይቀዋል።