ሱዳን ከነጻነቷ በኋላ ከባድ ቀውስ ውስጥ ገብታለች - ሃምዶክ
የቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ አድርገዋል
ሃምዶክ በሱዳን ጦር ከስልጣናቸው መነሳታቸው የሚታወስ ነው
የሱዳን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ሀገሪቱ ነጻነቷን ካወጀች ወዲህ እጅግ የከፋው ቀውስ ውስጥ መግባቷን ተናገሩ።
አብደላ ሃምዶክ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ አሁን ላይ የሚታየው ግጭት ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ለሰላማዊ አማራጮች አልረፈደም ያሉት ሃምዶክ፥ የሱዳን ወዳጆች ሀገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ ለማውጣት ሊረባረቡ ይገባል የሚል መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
ግጭቱ ሊበርድ የሚችለው ጦር የተማዘዙት ሃይላት ለንግግር ቦታ ሲሰጡ መሆኑን በመጥቀስም ካርቱም ለገባችበት ቀውስ ወታደራዊ መሪዎቹን ተጠያቂ አድርገዋል።
በሱዳን ኦማር ሀሰን አልበሽርን ከስልጣን ያነሳው ወታደራዊ ሃይል የሲቪል መንግስት ለመመስረት በገባው ቃል መሰረት አብደላ ሃምዶክ በነሃሴ ወር 2019 የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ ጦሩ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር በጥቅምት ወር 2021 ለቁም እስር ዳርጓቸው ነበር።
ጦሩ መፈንቅለ መንግስት አድርጎም ሃምዶክን ከስልጣን ማንሳቱ አይዘነጋም።
ይህም በሱዳን የሲቪል መንግስት ለመመስረት ሲደረግ የነበረውን ጥረት ወደኋላ መልሶታል።
ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመሩት ጦር የፈጸመውን የሲቪል አስተዳደር የማፍረስ ድርጊት የተቃወሙ ሱዳናውያንም አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
ተቃውሞው ሲበረታም ሃምዶክና ካቢኔያቸው ወደ ስልጣን መመለሱና የታሰሩ ባለስልጣናት መፈታታቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ለተቃውሞ የወጡ ሱዳናውያን ሃምዶክ “አብዮቱን ሽጡት” በሚል ቢቃወሟቸውም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ደም መፋሰሱን ለማቆም ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸው ነበር።
የሃምዶክ ወደስልጣም መመለስ ግን የሱዳንን የፖለቲካ ቀውስ ሊያበርደው አልቻለም።
ባለፉት ወራትም በሀገሪቱ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ይደረግ የነበረው ጥረት በጦሩና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ አለመግባባት ሳይሳካ ካርቱም ወደ ከፋ ቀውስ ገብታለች።