ዴሂያ ለዩናይትድ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች በ190ዎቹ ግብ ሳይቆጠርበት ወጥቷል
ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴሂያ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር መለያየቱን አረጋግጧል።
የ32 አመቱ ግብ ጠባቂ “አዲስ ፈተና ለማስተናገድ ጊዜው አሁን ነው” ብሏል።
ከዩናይትድ ጋር የሚያቆየው ውል በሰኔ ወር 2023 የተጠናቀቀው ዴሂያ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ የክለቡን ደጋፊዎች አመስግኖ ተሰናብቷል።
ፕሮፌሽናል ግብ ጠባቂነትን በአትሌቲኮ ማድሪድ የጀመረው ዴሂያ፥ በፈረንጆቹ 2011 ነበር ዩናይትድን በ18 ሚሊየን ፓውንድ የተቀላቀለው።
ባለፉት 12 አመታት ለቀያዮቹ ሰይጣኖች 545 ጊዜ ተሰልፎም በ190ዎቹ ግብ ሳይቆጠርበት ወጥቷል። ይህም በክለቡ ታሪክ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቦለታል።
ሁለት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን የወርቅ ጓንት ሽልማት የወሰደ ሲሆን አራት ጊዜ የአመቱ የዩናይትድ ኮከብ ተጫዋች ክብርን መቀዳጀቱም ይታወሳል።
ዴሂያ “በደጋፊዎች እና በክለብ አጋሮቹ የአመቱ ኮከብ ተጫዋች ክብርን ደጋግሞ ያሳካው ዴሂያ በክለቡ ታሪክ ሲታወስ ይኖራል” ብለዋል አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሃግ።
ከዩናይትድ ጋር የፕሪሚየር ሊግ፣ ኤፍ ኤ ካፕ እና ዩሮፓ ሊግ እንዲሁም ካራባዎ ዋንጫ ያነሳው ዴሂያ፥ መዳረሻው የሳኡዲ ሊግ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ዴቪድ ዴሂያ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር መለያየቱን ማረጋገጡን ተከትሎ ቴንሃግ የኢንተር ሚላኑን ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና የማስፈረም ጥረታቸውን ይገፉበታል ተብሏል።