የክረምት ወቅት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ዝውውር ገበያ እንደደራ ነው
የዲክላን ራይስን ጉዳይ የጨረሰው አርሰናል ተጨማሪ ተጫዎቾች ለማስፈረም ጥረቱን እንደቀጠለ ነው
አምና ብዙ ተጫዋቾችን በውድ ዋጋ የሸመተው ቸልሲ የአውሮፓን የፋይናንስ ህግ ላለመጣስ ተጫዋቾችን በመሸጥ ላይ ነው
የክረምቱ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ዝውውር ገበያ እንደደራ ነው።
የዘንድሮው ክረምት ከውድድር የጸዳ መሆኑ ክለቦች በነጻነት የፈለጉትን ተጫዎቾች ለማስፈረም ፉክክር ውስጥ ናቸው።
የሳውዲ አረቢያ እግር ኳስ ክለቦች በዘንድሮው የክረምት ዝውውር የተጫዋች ግዢ ላይ አዲስ ክስተት ሆነው ቀርበዋል።
ለወትሮው በአውሮፓ ክለቦች ብቻ ፉክክር ይደረግበት የነበረው የእግር ኳስ ተጫዋቾች የዝውውር ገበያ ዘንድሮ በነዳጅ ሀብት የበለጸገችው ሳውዲ አረቢያ ለተጫዋቾች ሲሳይ ሆነዋል።
በርካታ የአለማሽንን ተጫዋቾች በአጓጊ ደመወዝ እያማለሉ ያሉት የሳውዲ አረቢያ ክለቦች የሊቨርፑሉን ብራዚሊያዊ አጥቂ ሮቤርቶ ፍርሚንሆን ለማስፈረም ተስማምተዋል።
አል አህሊ ሮቤርቶ ፌርሚንሆን ለማስፈረም መስማማቱ ሲገለጸ ሌላኛው የሳውዲ ክለብ አል ናስር ደግሞ የኢንተሩን ክሮሺያዊ ተጫዋች ማርሴሎ ብሮዞቪችን ለመግዛት ከስምምነት ላይ ደርሷል።
በዘንድሮው የክረምት ዝውውር ንቁ ተሳትፎን እያደረገ ያለው የእንግሊዙ አርሰናል የዌስትሀሙን አማካኝ ዲክላን ራይስን ለመግዛት ተስማምቷል።
ነገ አልያም እሁድ የራይስን ዝውውር ለደጋፊዎቹ ያስተዋውቃል የተባለው አርሰናል ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ጥረት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
የአያክሱን ተከላካይ ቲምበርን ጥብቅ ፈላጊ የሆነው አርሰናል ከተጫዋቹ ጋር በግል መስማማቱ ሲገለጽ ከክለቡ ጋር ተጨማሪ ውይይቶች እየተደረጉ እንደሆነ ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
ሌላኛው የእንግሊዝ ክለብ ቼልሲ በውድ ዋጋ የሰበሰባቸውን ተጫዋቾች ለተለያዩ ክለቦች ዋሃ እየቀነሰ በመሸጥ ላይ ነው ተብሏል።
አርጀንቲናዊውን አሰልጣኝ ፖቼቲኖን የቀጠረው ቸልሲ ንጎሎ ክንቴ፣ ካይ ሀቨርትዝ፣ ሜንዲ፣ ሜሰን ማውንት፣ ኩሊባሊ እና ሌሎችንም ተጫዋቾች ሸጧል።
ክለቡ በውድ ዋጋ ብዙ ተጫዋቾችን ከዚህ በፊት መግዛቱ በአውሮፓ እግር ኳስ ክለብ ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት የለውም በሚል የተነሳበትን ጥርጣሬ ለማሳካት ሲል ተጫዋቾቹን ለመሸጥ መገደዱ ተገልጿል።
ሊቨርፑል በበኩሉ የክንፍ ተጫዋች የሆነው ካርቫልሆን ለጀርመኑ ላይፕዝሽ የሸጠ ሲሆን በምትኩ ደግሞ የዚሁ ክለብ አጥቂ የሆነውን ስዞቦዝላይን ለማስፈረም ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።
ሌላኛው የጀርመን ክለብ ባየር ሙኒክ የቶትንሀሙን የምንጊዜም አጥቂ ሀሪ ኬንን ለማስፈረም ግፊት ማድረጋቸውን ቀጥለውበታል ተብሏል።
የክለቡ የምንግዜም ኮኮብ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ቶትንሀም ኪንን ላይሸጠው እንደሚችልም ተገልጿል።
ሜሰን ማውንትን ለመግዛት ከቸልሲ ጋር ስምምነት ላይ የደረሰው ማንችስተር ዩናይትድ ተጨማሪ ተጫዋቾችን እንዲያስፈርም ከክለቡ ደጋፊዎች ግፊት እየተደረገበት ይገኛል።
የቀድሞው የባርሴሎና አሰልጣኝ ማርቲኖ የአሜሪካውን ኢንተር ሚያሚን ለማሰልጠን የተስማማ ሲሆን ክለቡን አስቀድመው የተቀላቀሉት የቀድሞዎቹ የካምፕኑ ተጫዋቾቹ ሊዮኔል ሜሲ እና ሰርጂዮ ቡስኬት ዳግም አብረው ይጫወታሉ ተብሏል።