በግድቡ ጉዳይ ሶስቱ አገራት ወደ ውይይት እንዲመለሱ ከማድረግ ውጪ ሊያደርግ የሚችለው ነገር እንደሌለ የጸጥታው ምክር ቤት አስታወቀ
በቀጣይ ሳምንትም በግድቡ ዙሪያ ዳግሞ ሊወያይ እንደሚችል ተገልጿል
ምክር ቤቱ በአረብ ሊግ እና በሱዳን ጥያቄ በግድቡ ዙሪያ ተወያይቷል
የጸጥታው ምክር ቤት በህዳሴው ግድብ ላይ ሶስቱ አገራት ወደ ውይይት እንዲመለሱ ከማድረግ ውጪ ሌላ መፍትሔ እንደሌለ ተገለጸ።
በወቅቱ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንትነት የተሰበሰበው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ዙሪያ መክሯል።
በመንግስታቱ ድርጅት የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላስ ደ ሪቬሪ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ላይ የገጠማቸውን አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱ ከማድረግ ውጪ ሌላ መፍትሄ እንደሌለ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ አክለውም “ምክር ቤቱ ሶስቱ አገራት ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ከማግባባት ባለፈ ሌላ የሚያደርገው ነገር አለ ብዬ አላስብም” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ምክር ቤቱ የተሰበሰበው ሱዳን፣ ግብጽ እና የአረብ ሊግ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ጣልቃ እንዲገባ በጠየቁት መሰረት አጀንዳ አድርገው ተወያይተዋል።
ምክር ቤቱ ከአንድ ሳምንት በኋላ በድጋሚ በግድቡ ዙሪያ ሊወያይ እንደሚችልም ዘገባው አክሏል።
ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በሶስቱ አገራት ዘንድ ያለው ልዩነት አፍሪካ ህብረት መር በሆነ ውይይት ብቻ ነው የሚፈታው ስትል ደጋግማ ማስታወቋ የሚታወስ ነው፡፡