ኢትዮጵያ የዐረብ ሊግ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ ውድቅ አደረገች
የአባይ ወንዝ የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብት እንጂ የግብጽና ሱዳን የግል ንብረት አይደለም- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የዓረብ ሊግ የተመድ የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቋል
የዐረብ ሊግ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የህዳሴ ግድብን አስመልክተው ያወጡት መግለጫ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ኢትዮጵያ አስታወቀች።
የዐረብ ሊግ አባል ሀገራት ትናንት በኳታር ዶሃ ባደረጉት ስብሰሳ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ጣልቃ እንዲገባ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ ውሳኔን ሙሉ በሙሉ እንደማትቀበል አስታውቋል።
የአረብ ሊግ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴን በተመለከት የተሳሳተ ውሳኔ ሲያሳልፍ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ያለው ሚኒስቴሩ፤ ይህም ግብፅ እና ሱዳን በግድቡ ላይ ለሚያነሱት መሰረተ ቢስ ጥያቄ ያለውን ድጋፍ ለማመላከት የሚያድርገው መሆኑን ገልጿል።
ሊጉ በግድቡ ዙሪያ ሊጫወት የሚገባውን ገንቢ ሚና ቀድሞ አባክኖታል ያለው ሚኒስቴሩ፤ የግድቡን ጉዳይ ዓለማቀፋዊ ለማድረግ የሚደረጉ ሙከራዎች የዓባይ ውሃ አጠቃቀም እና ቀጠናዊ ትብብርን ዘላቂ የማያደርጉ ናቸው ብሏል።
የአባይ ውሃን መጠቀም ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የአረብ ሊግ አባል ሀገራት ሊረዱት ይገባል ያለው ሚኒስቴሩ፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከድህነት የማውጣት እና ሀይል ፍላጎታቸውን የማሟላት ጉዳይ እንደሆነም አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ህጎች እና መርህዎችን ባከበረ መልኩ የውሃ ሀብቷን እየተጠቀመች ነው ያለው መግለጫው፤ የአባይ ውሃ አጠቃቀም እና የተፋሰሱ ሀገራት ደህንነት ሊጠበቅ የሚችለው በትብብር እና በንግግር ብቻ ነው ብሏል።
የአባይ ወንዝ የተፋሰሱ ሀገራት ጋራ ሀብት እንጂ የግብጽ እና ሱዳን የግል ንብረት አይደልም ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው።
ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ስጋቶችን ለመቅረፍ የሚቻላትን ሁሉ ማድረጓንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
በህዳሴ ግድበ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች ትርጉም ያለው ስምምነት ላይ እንዳይደርስም ግብጽ እና ሱዳን እንቅፋት ሲሆኑ መቆታቸውን አስታውቋል።
በደቡብ አፍሪካ መሪነት በግድቡ ዙሪያ ሲደረግ በነበረው ድርድር ላይ ሱዳን እና ግብጽ ድርድሩን ለሰባት ጊዜ ማደናቀፋቸውን በማንሳት፤ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሪነት የሚደረገው ድርድርም ውጤት እንዳያመጣ እየሰሩ መሆኑንም አስታውቋል።
በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚደረገውን ድርድር በሚገባ ሳያጤኑ የአረብ ሊግ አባል ሀገራት የሳለፉትን ውሳኔ ኢትዮጵያን እንዳሳዘናት እና ሊጉ ውሳኔውን ዳግም ሊያጤነው እንደሚገባም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ሀገራቱ በአውሮፓውያኑ በ2015 በተፈራረሙት የስምምነት መርህ መሰረት እንደሚከናወን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፤ የአረብ ሊግ የግድቡን ሙሌት አስመልክቶ ያነሳውን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ እንደማትቀበልም አስታውቃለች።
ግብጽ እና ሱዳን የግድቡን ጉዳይ ፖለቲካዊ እና የአረብ ሀገራት ጉዳይ ለማድረግ የሚሄዱት መንገድ እትዮጵያ ማሳዘኑን እና የግድቡ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ ብቻ እንደሆነም አስታውቋል።
ከግድቡ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና በሱዳን መካከል ያለው አለመግባባት የሚፈታው በመተማመን ላይ በተመሰረት ውይይት እና በአፍሪካዊ መፍትሄ ብቻ እንደሆነም ተገልጿል።
በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ላይ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚደረገውን ድርድር የአረብ ሊግ አባል ሀገራት በሚገባ ሳያጤኑ ያደረጉትን ሚዛናዊነት የጎደለው ውሳኔ በድጋሜ እንዲመለከቱትም መግለጫው አብራርቷል።
የዐረብ ሊግ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት በኳታር ዶሃ ባደረጉት ስብሰባ በአፍሪካ ሕብረት ስር እየተካሄደ ያለው ድርድር አዝጋሚ በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በግድቡ ዙሪያ ስብሰባ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የሊጉ አባል ሀገራት ግድቡን በተመለከት የሁሉንም አካላት ፍላጎት የሚያሳካ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መደረስ እንዳለበት ማንሳታቸውም ይታወሳል።