ተርባይኖቹ በድምሩ 700 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አላቸው ተብሏል
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የፊታችን ነሀሴ ወር 700 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንደሚጀምር ተገለጸ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ትናንት 10 ዓመት ሞልቶታል።
የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ግድቡ የተጀመረበትን 10ኛ ዓመት አስመልክተው እንደተናገሩት የግድቡ ሁለት ተርባይኖች በመጪው ነሀሴ 2013 ዓ.ም ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫት ይጀምራሉ።
ተርባይኖቹ እያንዳንዳቸው 350 ዋጋ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም እንዳላቸው መነገሩ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት “ሁለቱ ተርባይኖች ሀይል እንዲያመነጩ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች በፍጥነት በመከናወን ላይ” ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ ከነሀሴ በፊት ሁሉንም ስራዎች እናጠናቅቃለን ብለዋል።
የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በመጭው ክረምት እንደሚጀመርም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የህዳሴ ግድብ ድርድር የሶስቱ አገራት ውሃ ሚኒስትሮች፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራን እና ታዛቢዎች በተገኙበት በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳነት ፊሊፕ ሼስኬዲ አደራዳሪነት ዛሬ በኪንሻሳ ከተማ ይካሄዳል።
በድርድሩ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን ሚኒስትሮች፣ ምሁራን እና ዲፕሎማቶች ወደ ስፍራው ማቅናታቸው ተሰምቷል።