ለሞት እጅ አልሰጥም ያሉት አዛውንት ከአስከሬን ሳጥን አንኳኩተው ወጥተዋል
በኢኳዶር “ሞተዋል” ተብለው ሊቀበሩ የነበሩት የ76 አመት አዛውንት በአስከሬን ሳጥን ውስጥ በሃይል እየተነፈሱ ተገኝተዋል
የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ክስተቱን የሚያጣራ ኮሚቴ አዋቅሯል
በኢኳዶር የ76 አመቷ ቤሊያ ሞንቶያ ህይወታቸው አልፎ ወዳጅ ዘመድ ተሰብስቧል።
ልጃቸው ጊልበር ሮዶልፎም “ሟች” እናቱን ማጣቱ አንገብግቦት በሀዘን ስብር ብሎ ተቀምጧል።
ሞንቶያ “ህልፈታቸው” በሀኪሞች ተረጋግጦ ቤተሰቡ ከተረዳ ከአምስት ስአት በኋላ ግን ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ።
አዛውንቷ የተቀበሩበት የአስከሬን ሳጥን አካባቢ ድምጽ መስማት ጀመረ።
ለ”ሟቿ” ልብስ ለመቀየር ወደ ሳጥኑ የተጠጉ ቤተሰቦችም ድምጹን ብቻ ሳይሆን አዛውንቷ ትንፋሿ እንዳልተቋረጠ አረጋገጡ።
እናም በፍጥነት ወደህክምና ተቋም ተወስደው ለቀብር የተሰባሰበው ቤተሰብም ወደየመጣበት ተመልሷል።
በስትሮክ ህመም ህይወታቸው ማለፉን ያረጋገጠው ሀኪምና ሆስፒታሉ ምርምራ እንዲደረግባቸው የኢኳዶር ጤና ጥበቃ ሚኒሲቴር አስታውቋል።
ሞንቶያ ልባቸው መምታት፣ በሰው ሰራሽ መሳሪያም መተንፈስ አቁመው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ ሊቀበሩ ሲሉ የመንቃታቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ያነጋገረው ልጇ ጊልበር ሩዶልፎ፥ እናቱ ጤናቸው እንዲመለስ በመጸለይ ላይ መሆኑን ገልጿል።
ክስተቱ ህይወታቸው ማለፉ ተነግሮ በፍጥነት ወደ አስከሬን ሳጥን የተወረወሩና የሚያደምጣቸው አጥተው ነፍሳቸው ሳይወጣ የተቀበሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል እንደማይሆን ያሳያል ተብሏል።