ዶናልድ ትራምፕ ከተከሰስኩ በአሜሪካ ሞትና ውድመት ይከሰታል ሲሉ አስፈራሩ
ትራምፕ ከአንዲት ተዋናይት ጋር የነበራቸውን ግንኙነትን ለመደበቅ ገንዘብ ከፍለዋል በሚል ሊከሰሱ ይችላሉ ተብሏል
የአሜሪካ ፖሊስ ሊፈጠር የሚችለውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር በተጠንቀቅ ላይ ነው
አወዛጋቢው የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተከሰስኩ በአሜሪካ ሞትና ውድመት ይከሰታል ሲሉ ማስፈራራታቸው ተሰምቷል።
ትራምፕ ከአንዲት ተዋናይት ጋር የነበራቸውን ግንኙነትን ለመደበቅ ገንዘብ ከፍለዋል በሚል ሊከሰሱ ይችላሉ ተብሏል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንት እንደሚታሰሩ ከተነገረ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ባስተላለፉት መልእክት ደጋፊዎቻቸው ለተቃውሚ እና ለአመጽ እንዲወጡ መግለጻቸው ይታወሳል።
በ2024 በድጋሚ አሜሪካን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት እንደሚወዳደሩ ያስታወቁት ዶናልድ ትራምፕ፣ የምታሰርና የምክሰስ ከሆነ በአሜሪካ ምድር ሞትና ውድመት ይከሰታል ሲሉ ዝተዋል ነው የተባለው።
ትራምፕ በተጨማሪም የማንሃተን አቃቤ ህግ ቢሮ እና ጉዳያቸውን የያዘው ዋና አቃቤ ህግ አልሺን ብራግ ላይ ተአጋጋሚ ዛቻዎችን ሲዘነዝሩ ነበረ ተብሏል።
ትራምፕ አስተያየትን ተከትሎ በርካታ ደጋፊዎቻቸው ወደ ዐቃቤ ህግ አልቪን ብራግ 'እገልሃለሁ' የሚልን ጨምሮ በርካታ የማስፈራሪያ መልእክቶች እንዲሁም ነጭ ዱቄት የያዙ የፖስታ መልእክቶች መድረሳቸው ተሰምቷል።
የህግ አካላት በደብዳቤው ላይ ባደረጉት ማጣራት በዱቄቱ ውስጥ ጎጂ ነገር አለመገኘቱን አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ፖሊስ ከትራምፕ መከሰስ ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችለውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር በተጠንቀቅ ላይ መሆኑ አስታውቋል፡፡
በዚህም በኒውዮርክ፣ ዋሽንግተን ዲሲ እና ሎስ አንጀለስ ያለው የፖሊስ ኃይሎች ስምሪት መጠናከሩ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ትራምፕ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ከሆነ የማንሃታን አቃቤ ህግ ከአንዲት የወሲብ ፊልም ተዋናይት ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና ተዋናይዋን ዝም ለማስባል ገንዘብ ከፍለዋታል የሚል ክስ ሊመሰርት ይችላል ተብሏል፡፡
ትራምፕ በተባለው የወንጀል ድርጊት የሚከሰሱ ከሆነ በአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ በእንዲዘህ አይነት ቅሌት የተከሰሱ የመጀመሪያው መሪ መሆናቸው ነው፡፡