በ5 ወሯ የተወለደችው እንግሊዛዊ በአስደናቂ ሁኔታ ከሞት ተረፈች
ከመደበኛ የመወለጃ ጊዜዋ 126 ቀናት ቀድማ የተወለደችው ህጻን ከአራት ወራት የህክምና ክትትል በኋላ በእናቷ እቅፍ ውስጥ ገብታለች
በአለማችን ያለጊዜው ተወልዶ በህይወት በመትረፍ ክብረወሰኑን የያዘው በ21 ወሩ የተወልደው ክሪስ ኬት ሚንስ የተባለ አሜሪካዊ ህጻን ነው
በህይወት የመቆየት እድሏ ከ10 በመቶ በታች እንደሚሆን የተገመተችው እንግሊዛዊ ህጻን ለሞት እጅ አልሰጥም ብላለች።
ከተጸነሰች በ22 ሳምንቷ (154 ቀን) የተወለደችው “ኢሞጀን” የተሰኘች ህጻን ግምቶችን ውድቅ አድርጋ ከ132 ቀናት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ በእናቷ እቅፍ ውስጥ ሆናለች።
ኢሞጀን እናቷ ሪቼል ስቶንሃውስ በድንገተኛ ህመም ወደሆስፒታል አቅንታ መወለድ ከነበረባት 126 ቀናት አስቀድማ ስትወለድ 515 ግራም ትመዝን ነበር።
በእናቷ ማህጸን እድገቷን ሳትጨርስ ስዋንሲ ሲንግልተን በተባለ ሆስፒታል መወለዷ ግድ የሆነው ህጻን፥ ወዲያውኑ ሰው ሰራሽ ማሕጸን ውስጥ እንድትገባ ተደርጎ ክትትል ይደረግላት ጀመር።
ሀኪሞችም የህጻኗ የመትረፍ እድል ከ10 በመቶ በታች እንደሆነ ቢያውቁም ተስፋ ሳይቆርጡ ለ132 ቀናት የዘለቀ ድንቅ ጥረታቸውን ቀጠሉ።
ያለጊዜዋ የተወለደችው ኢሞጀን በጽኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ ሆና ያሳለፈችውን ስቃይ ማየት እጅግ ሰቅጣጭ ነበር የምትለው እናቷ ሪቸል፥ “ልጄ እኛ ትልልቆቹ የማናልፈውን ፈታኝ ጊዜ አሸንፋ አልፋዋለች፤ ያመንኳቸው የህክምና ባለሙያዎችም አላሳፈሩኝም” ብላለች።
ሪቼል በማህጸኗ ውስጥ የሚገባትን ማግኘት ያልቻለችውንና የገጠማትን የልብ ህመም ጭምር ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ባለሙያዎችም አመስግናለች።
ሪቸል እና ባለቤቷ በአስደንጋጩ ክስተት ምክንያት የአዕምሮ መቃወስ እንዳይገጥማቸው ለሶስት ወራት በሆስፒታሉ ውስጥ ማረፊያ ተዘጋጅቶላቸው የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።
በ22 ሳምንቷ ተወልዳ፤ በብዙ ስቃይ ውስጥ አልፋ ከሆስፒታል የወጣችው ኢሞጀን አሁን በወላጆቿ እንክብካቤ እየተደረገላት ነው።
ለመተንፈስ ስለምትቸገር ኦክስጂን የሚያስፈልጋት ቢሆንም ማየትም ሆነ መስማት መቻሏ እና የከፋ የጤና ችግር የለባትም መባሉም ከ4 ወራት በላይ በስቃይ ላሳለፉት ወላጆች ትልቅ ደስታን ፈጥሯል።
በአለማችን ያለጊዜው ተወልዶ በህይወት በመትረፍ ክብረወሰኑን የያዘው ክሪስ ኬት ሚንስ የተባለ አሜሪካዊ ህጻን ነው።
ክሪስ በአላባማ በርሚንግሃም ሆስፒታል በ21 ሳምንት ከ1 ቀኑ (ከተጸነሰ በ148 ቀናት) ሲወለድ 420 ግራም ይመዝን የነበረ ሲሆን፥ የመትረፍ እድሉም ከ1 በመቶ በታች ነው ተብሎ ነበር።
ክሪስም ሆነ ኢሞጀን ግን ሞትን ታግለው ሳይንሳዊ ግምቶችን መሻር ችለዋል።