በምያንማር ትናንት በትንሹ 114 ሰላማዊ ሰልፈኞች ተገደሉ
የአሜሪካን ጨምሮ የ12 ሀገራት የጦር ኢታማዦር ሹሞች የምያንማርን ጦር በማውገዝ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል
እስካሁን የሟቾች ቁጥር ከ440 የበለጠ ሲሆን የሀገሪቱ ጦር በበርካታ ሀገራት እየተወገዘ ነው
የምያንማር ጦር በመፈንቅለ መንግስት የሀገሪቱን ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ የተቃውሞ ሰልፎች የቀጠሉ ሲሆን የፀጥተ ኃይሎችም በሰልፈኞቹ ላይ የሚወስዱት እርምጃ እንደቀጠለ ነው፡፡
በትናንትናው ዕለት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ በተወሰደ እርምጃ በትንሹ 114 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡ ይህም እንደ አውሮፓውያኑ የካቲት 1 ከተካሔደው መፈንቅለ መንግስት ወዲህ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር ነው፡፡
በሀገሪቱ ዓመታዊ የጦር ኃይሎች ቀን ፣ ቅዳሜ እለት የተመዘገበውን ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር ጨምሮ ፣ እስካሁን በመፈንቅለ መንግስቱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ440 በልጧል፡፡
ከትናንተናው ግድያ በኋላ የምያንማር ጦር ከመላው ዓለም ከፍተኛ ውግዘት እየገጠመው ነው፡፡ ቅዳሜ እለት በተፈጸመው ግድያ “ዋሺንግተን ደንግጣለች” ያሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ፣ ድርጊቱ “ጁንታው ጥቂቶችን ለማገልገል ህዝቡን እንደሚሰዋ አመላካች ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡
“ለተጎጂ ቤተሰቦች የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልፃለሁ፡፡ ደፋሩ የበርማ ህዝብ የወታደራዊውን የሽብር ዘመን አይቀበልም” ሲሉም አክለዋል፡፡
የአሜሪካ ፣ የዩኬ ፣ የካናዳ እና የጀርመንን ጨምሮ የ12 ሀገራት የጦር ኢታማዦር ሹሞችም “የምያንማር ጦር በህዝቡ ታማኝነት አጥቷል” በማለት ጦሩን በማውገዝ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
መግለጫው “የመከላከያ ኃላፊዎች እንደመሆናችን መጠን በምያንማር ታጣቂ ኃይሎች እና በተጓዳኝ የፀጥታ አካላት ባልታጠቁ ሰዎች ላይ የመግደል እርምጃ መወሰዱን እናወግዛለን” ብሏል፡፡
የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ ሀገራትና ድርጅቶች የምያንማርን ጦር አውግዘዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ልዩ ዘጋቢ ቶም አንድሪውስ “ዓለም እርምጃ መውሰድ ያለበት ጊዜ አሁን ነው” ሲል ተናግሯል፡፡ አክሎም “በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት በኩል ፣ ካልሆነ ደግሞ በዓለም አቀፍ አስቸኳይ ስብሰባ፣ ጁንታው የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኝ እና የመሣሪያ ተደራሽነት እንዳይኖረው ማድረግ ያስፈልጋል” ብሏል፡፡
“የውግዘት ቃላት ብቻ በቂ አይደሉም” ያለው አንድሪውስ “የምያንማር ህዝብ ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ጠንካራ እና የተቀናጀ እርምጃ እና ድጋፍ ይፈልጋል” ሲልም ነው የገለጸው፡፡
የምያንማር ገዢ የነበረው የኦንግ ሳን ሱ ቺ ፓርቲ በህዳር ወር የተካሄደውን ምርጫ አጭበርብሮ ማሸነፉን በመግለጽ ነበር የሀገሪቱ ጦር በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቆጣጠረው፡፡ ጦሩ ተለዋጭ ምርጫ አደርጋለሁ ቢልም የህዝቡን ተቃውሞ ማስታገስ ግን አልቻለም፡፡