ትናንት በተከበረው የምያንማር ‘የመከላከያ ሰራዊት ቀን’ 16 ሰዎች ሳይገደሉ አልቀረም ተባለ
ሳን ሱ ኪ በቁጥጥር ከዋሉበት ከካቲት 1 አንስቶ ምያንማር በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ እየተናጠች ትገኛለች
የሀገሪቱ ወታደራዊ አዛዡ ሚን አውንግ ህላይንግ “በቀጣይ ምርጫ ይካሄዳል ስለዚህም ማንኛውም አይነት አመጽ የተከለከለ ነው” ሲሉ አሳስበዋል
‘የመከላከያ ሰራዊት ቀን’ በተከበረበት በትላንትናው እለት በምያንማር ቢያንስ 16 ሰዎች ሳይገደሉ አልቀረም ተባለ፡፡
ሰዎቹ የተገደሉት አከባበሩን ተቃውመው መውጣታቸውን ተከትሎ ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ነው፡፡
በዚህም በሀገሪቱ መዲና ያንጎን 11፤ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በምትገኘው የላሽዮ ከተማ 4፣ እንዲሁም በደቡባዊቷ የባንጎ ከተማ 1 ሰው በድምሩ 16 ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል፡፡
አንዳንድ ዘገባዎች ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር ከዚህ ከፍ ያለ ያደርጉታል፡፡
በወታደራዊ በዓሉ አከባባር ላይ ንግግር ያደረጉት የሃሪቱ ጦር ኃይሎች መሪ ሚን አውንግ ህላይንግ “በቀጣይ ምርጫ ይካሄዳል ስለዚህም ማንኛውም አይነት አመጽ የተከለከለ ነው” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በሳን ሱ ኪ ይመራ የነበረውና በአሁኑ ወቅት ከስልጣን የተባረረው የሃገሪቱ መሪ ፓርቲ ብሄራዊ ሊግ ለዴሚክራሲ (NLD) “ህገ ወጥ ድርጊቶች” ተከትሎ ወታደራዊ ኃይሉ ባለፈው የካቲት 1 ወደ ስልጣን መምጣቱን የተናገሩት ያሉት ወታደራዊ አዛዡ በቁጥጥር ስር በዋሉትና በሙስና በተጠረጠሩ አመራሮች ላይ ህጋዊ እርመጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጦር ኃይሉ በወርሃ ህዳር የተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ “ተጭበርብረዋል” በሚል ምክንያት ሳን ሱ ኪን እና ሌሎች ከፍተኛ የሃገሪቱን ባለስልጣናት ካሰረበት ጊዜ ጀምሮ ምያንማር በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ እየተናጠች ትገኛለች ፡፡
እስካሁን 149 ዜጎች ለሞት መዳረጋቸውንም ነው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት መጋቢት 17 ያወጣው መረጃ የሚያመላክተው፡፡