ግለሰቦቹ ኮሮናን ለመቆጣጣር ከወጣው አዲስ የእንቅስቃሴ እገዳ ጋር በተያያዘ በሚኒስትሩና ቤተሰባቸው ላይ ይዝቱ ነበር ተብሏል
በጤና ሚኒስትር ሮቤርቶ ስፔራንዛ ላይ የግድያ ዛቻዎችን ያደርጉ ነበር የተባለላቸው 4 ጣሊያናውያን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
ጣሊያናውያኑ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጣር ከወጣው አዲስ የእንቅስቃሴ እገዳ ጋር በተያያዘ በሚኒስትሩና በቤተሰባቸው ላይ እንደሚገድሏቸው ጭምር በግልጽ ይዝቱ ነበር ተብሏል፡፡
ከወርሃ ጥቅምት እስከ ጥር ባሉት ጊዜያት ተደጋጋሚ ማስፈራሪያዎች ግልጽ የግድያ ዛቻዎች ጭምር በኢ-ሜይል ይደርሷቸው እንደነበርም ነው ፖሊስ የገለጸው፡፡
ዛቻዎቹ ይተላለፉባቸው የነበሩ ናቸው ያላቸውን ኮምፒውተሮችና ሌሎች መገልገያ ቁሳቁሶችን መያዙንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ጤና ሚኒስትሩ ላይ ይዝቱ የነበሩት በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች የሚኖሩና ከ35 እስከ 55 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 4 ጣልያናውያን ናቸው እንደ ፖሊስ ገለጻ፡፡
በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡
ስፔራንዛ ዳግም አገርሽቶ የብዙዎችን ህይወት እየቀጠፈ ያለውን የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት ለመቆጣጠር በሚል ጥብቅ የእንቅስቃሴ እገዳዎች እንዲጣሉ በጽኑ ከሚጠይቁ የጣሊያን መንግስት ከፍተኛ አመራሮች መካከል ናቸው እንደ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ፡፡
በአደገኛ የቫይረሱ ሁኔታዎች ውስጥ እንደምትገኝ የተነገረላት ሃገራቸው ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ፋሲካ ሰኞ ድረስ በዚህ ጥብቅ የእንቅስቃሴ እገዳ ውስጥ ሆና እንድታሳልፍም አዘዋል፡፡
ይህ እርምጃቸውን በተቃወሙ ጣሊያናውያን ክፉኛ እያስተቻቸው ነው፡፡
የቀደሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒትር እና የናሽናሊስት ሊግ ፓርቲ መሪው ማቲዎ ሳልቪኒ ሳይቀሩ “እገታ ነው” በሚል ይህን የስፔራንዛን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡
3 ነጥብ 6 ሚሊዬን ሰዎች በኮሮና በተያዙባት ጣሊያን በአሁኑ ሰዓት ከ560 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ይገኛሉ፡፡
2 ነጥብ 9 ሚሊዬን ገዳማ የቫይረሱ ተጠቂዎች ሲያገግሙ 110 ሺ ገደማ ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ነው፡፡