በአሜሪካ በአንድ ቀን ብቻ 5,000 የኮሮና ተጠቂዎች ሲገኙ ካሊፎርኒያ 40 ሚሊዮን ነዋሪዎቿ ከቤት እንዳይወጡ አግዳለች
በአሜሪካ በአንድ ቀን ብቻ 5,000 የኮሮና ተጠቂዎች ሲገኙ ካሊፎርኒያ 40 ሚሊዮን ነዋሪዎቿ ከቤት እንዳይወጡ አግዳለች
ጣሊያን በኮሮና ቫይረስ በሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዓለም አንደኛ ሆነች
በቻይና እስካሁን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት 3ሺ 253 ዜጎች የሞቱ ሲሆን ይህም ከየትኛውም ሃገር የበለጠ ቁጥር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና አሁን ላይ ቫይረሱ በጣሊያን ለ 3ሺ 405 ዜጎች ሞት ምክኒያት መሆኑ ተሰምቷል፡፡በጣሊያን ያለው የሟቾች ቁጥርም ቫይረሱ ከተቀሰቀሰባት ቻይና በ152 በልጧል፡፡ በ24 ሰዓት ውስጥ በጣሊያን 427 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን ይህም ከሌሎች ቀናት ቁጥሩ መጨመሩን ያሳያል፡፡
በዓለም የኮሮና ስርጭት (WHO መጋቢት10)
በጣሊያን ከቫይሱ መዛመት ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶች፣ቴአትር ቤቶች፣ የህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎችና ሌሎች እንቅስቃሴዎች መታገዳቸው ይታወቃል፡፡ በሃገሪቱ የግሮሰሪና የመድሃኒት መደብሮች ብቻ ናቸው ክፍት እንዲሆኑ የተፈቀደው፡፡ ዜጎች ራሳቸውን በለይቶ ማቆያ የሚያቆዩበት ጊዜ በፈረንጆቹ ሚያዚያ 3 ይጠናቀቃል ቢባልም ሊራዘም እንደሚችል ይገመታል፡፡
ካሊፎርኒያ 40 ሚሊዮን ነዋሪዎቿ ከቤት እንዳይወጡ አገደች
የካሊፎርኒያ ገዢ ጋቪን ኒውሰም በአሜሪካ የመጀመሪያውን ግዛት አቀፍ እገዳ ባወጁበት ወቅት እንዳሉት፣ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት ነው እርምጃው የተወሰደው፡፡ አዋጁ ከትናንት ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በአሜሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለው የካሊፎርኒያ ግዛት እስካሁን በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ ከ900 በላይ ሰዎች መካከል የ 19ኙ ህይወት አልፏል፡፡
በአሜሪካ በአንድ ቀን ብቻ 5,000 የኮሮና ተጠቂዎች ተገኙ
ሀገሪቱ በ24 ሰዓታት ውስጥ 5,000 ተጠቂዎችን ማግኘቷን የገለጸች ሲሆን ይሄም አጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎቿን ቁጥር ከ14,000 በላይ አድርሷል፡፡ ሁለት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሀገሪቱ የተለዩ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር በእጥፍ አድጓል፡፡ የዋይት ሀውስ የኮሮና ቫይረስ መከላከል አስተባባሪ ዶ/ር ዲቦራ ቢርክስ እንዳሉት በቀጣዮቹ 3 ቀናትም በአሜሪካ የተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ሊጨምር ይችላል፡፡ እስካሁን በልዕለ ሀያሏ ሀገር ከ250 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡
ቻይና ለ ሁለተኛ ተከታታይ ቀን በሀገሯ የኮሮና ተጠቂ እንዳላገኘች አስታወቀች
የኮሮና ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተባት ቻይና ትናንት ለ ሁለተኛ ቀን ምንም የኮሮና ቫይረስ ታማሚ አለማግኘቷን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡ ምንም እንኳን 39 የቫይረሱ ተጠቂዎች በ24 ሰታዓት ውስጥ ቢለዩም ሁሉም ተጠቂዎች ከውጭ ሀገራት የመጡ ናቸው ተብሏል፡፡ ሀገሪቱ በትናንትናው እለት 3 ሞት አስተናግዳለች፡፡ ባጠቃላይ በሀገሪቱ እስካሁን ከተለዩ 81,300 የቫይረሱ ተጠቂዎች 3,253 ሰዎች ሲሞቱ 71,150 ሰዎች ደግሞ አገግመው ከሆስፒታል ወጥተዋል፡፡
ኢራናውያን በአዲሱ ዓመት አንድነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኃይማኖታዊ መሪው ጥሪ አቀረቡ
የኢራኑ እስላማዊ አብዮት መሪ አያቶላህ አሊኻሚኔይ ዛሬ የገባውን የኢራናውያኑን አዲስ ዓመት አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ኢራናውያን በአሜሪካ ማዕቀብ ቢፈተኑም፣ ብዙ መከራን ቢያሳልፉም በዚያው ልክ ብዙ አትርፈዋል ራሳቸውን ችለው አሳይተዋልም ብለዋል፡፡ አዲሱ ዓመት የመትረፍረፍ እንዲሆን የተመኙት ኻሚኔይ ኢራናውያን አንድነታቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ ስለማሳሰባቸው ፕሬስ ቲቪ ዘግቧል፡፡ ከ18400 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁባት ቴህራን 1 ሺ 3 መቶ ገደማ ዜጎቿን በኮሮና ወረርሽኝ መነጠቋ የሚታወስ ነው፡፡ ሀገሪቱ በአሜሪካ የተጣለባት ማዕቀብ አስፈላጊ የህክምና ቁሳቁሶችን በግዢ እናዳታስገባ ማድረጉ ፈተናዋን እንዳባባሰባት ይታመናል፡፡
ሳዑዲ የሃገር ውስጥ ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን አገደች
ሳዑዲ አረቢያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚል በሃገር ውስጥ የሚደረጉ ሁሉንም የአየርና የየብስ ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 14 ቀናት ማገዷን ሳዑዲ ፕሬስ ኤጄንሲ ዘግቧል፡፡ ከሰብዓዊነት ጋር የተያያዙ አስፈላጊ እንዲሁም የህክምና አውሮፕላኖችና የግል አየር መንገዶች ብቻ ከሃገሪቱ አቪዬሽን ባለስልጣን በሚገኝ ፍቃድ መብረር እንደሚችሉም ዘገባው አትቷል፡፡ እስካሁን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምንም ዓይነት ሞት ባልገጠማት ሳዑዲ 247 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ቫይረሱን ለመከላከል ዓለማቀፍ ትብብር ሊጠናከር ይገባል አሉ
ቻይና የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሁሉም የኣለም ሀገራት ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኗን ፐሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ተናግረዋል፡፡ ሲጂቲኤን እንደዘገበው ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ትናንት ምሽት በስልክ ውይይት ያደረጉት የቻይና ፕሬዝዳንት ቫይረሱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ቻይና በልዩ ትኩረት ስርጭቱን ለመቆጣጠር ርብርብ ማድረጓን በመግለጽ ሀገራቸው ለቻይናውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ህዝብ ጤና እንደምትጨነቅ ተናግረዋል፡፡ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ከተባበረ ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር እንደሚቻል ቻይና ሙሉ እምነት እንዳለትም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ቻይና ቫይረሱን ለመቆጣጠር የወሰደችውን ጠንካራ እርምጃ ያደነቁት የሩሲያው ፕሬዝዳንት፣ የሀገሪቱ ያላሰለሰ ጥረት ለሌሎች ሀገራትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ቻይና ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት እንደምትሆንም ነው ፕሬዝዳንት ፑቲን የገለጹት፡፡
በአሁኑ ወቅት በቻይና የቫይረሱ ስርጭት እየተገታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ህይወት ወደ ቀድሞ ስፍራው እየተመለሰ ይገኛል፡፡ ቻይና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራትን ጨምሮ ለበርካታ ሀገራት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከቁሳቁስ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ያደጉ ሃገራት ለኮሮና ተጋላጭ ሃገራት ድጋፍ እንዲያደርጉ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጠየቁ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ያደጉ ሃገራት ለኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ሃገራት እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ፡፡ ዋና ጸሐፊው ከዋና መስሪያ ቤታቸው ኒውዮርክ ሆነው በሰጡት የቪዲዮ መግለጫ ያደጉ ሃገራት በተለይም የቡድን 20 አባል ሃገራት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ ለሆነባቸውና በግዛቶቻቸውም የቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች ላሉባቸው ሃገራት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በተመድ የ 75 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ፈተና ያጋጠመው አሁን ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው ይህም የሰዎችን ህይወት በመቅጠፍና የዓለምን ኢኮኖሚ በማዳከም ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ነው ብለዋል፡፡
የኮሮና ሟቾች ቁጥር ከ10 ሺ በልጧል
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ባጠቃላይ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 250 ሺ ገደማ ሲደርስ የሟቾቹ ቁጥር ደግሞ ከ 10ሺ በልጧል፡፡
ለዘገባው የዓለም ጤና ድርጅት እና የተለያዩ የዜና ምንጮችን በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡