ጣሊያን “ሰነዶችን ሊያሸሹ ነበር” ያለቻቸው ሁለት የሩሲያ ዲፕሎማቶችን አባረረች
ቡልጋሪያ እና ኔዘርላንድስ በቅርቡ በተመሳሳይ ድርጊት የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ማባረራቸው የሚታወስ ነው
ሞስኮ “ሆኗል” በተባለው ሁሉ ደስተኛ ባትሆንም “የሁለትዮሽ ግንኙነቱ አይበላሽም” ብላለች
ጣሊያን ሁለት የሩሲያ ዲፕሎማቶችን አባረረች፡፡
ዲፕሎማቶቹ የተባረሩት ከአንድ የጣሊያን ባህር ኃይል ካፒቴን በአንድ ድብቅ ስብሰባ ላይ ሰነዶችን ሲቀበሉ በፖሊስ በመያዛቸው ነው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ሊያዙ የቻሉት በሮማ ዐቃቤ ህጎች ትዕዛዝ የሃገሪቱ የደህንነት ተቋም ባደረገው ረጅም ምርመራ ነው፡፡
ካፒቴኑ ለሩሲያ ባለስልጣናት ሊያስተላልፍ የነበረው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ጥብቅ ሚስጥራዊ ወታደራዊ ሰነዶችን ሳይሆን እንዳልቀረ ተጠርጥሯል፡፡
ሌሎች ምዕራባዊ የኔቶ አባል ሃገራትን ሁሉ ከፍተኛ ስጋት ላይ በጣለው በዚህ ድርጊትም ጣሊያናዊው ካፒቴን እና በኤምባሲው እውቅና የተሰጠው አንድ ሩሲያዊ ወታደራዊ ባለስልጣን ተከሰዋል፡፡
ክሱ “ከስለላ እና ከስቴት ደህንነት ጋር በተያያዙ ከባድ ወንጀሎች ተጠርጥረዋል” በሚል የቀረበ ነው፡፡
ሆኖም የተጠርጣሪዎቹ ማንነት በስም አልተገለጸም እንደ ሮይተርስ ዘገባ፡፡
ድርጊቱን ተከትሎም የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊጂ ዲ ማዮ ወዲያውኑ የሩሲያ አምባሳደር ሰርጌ ራዞቭን ጠርተው አናግረዋል፡፡
ዲ ማዮ “እጅግ በጣም ከባድ ነው” ባሉት ጉዳይ በድርጊት ተሳትፈዋል የተባሉ ሁለት የሩሲያ ባለስልጣናትን ማባረራቸውን ነው ለአምባሳደሩ የገለጹት፡፡
ጣሊያናዊው የባህር ኃይል ካፒቴን እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
“ሞስኮ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ተመጣጣኝ መልስ የመስጠት ልምድ አላት” ሲል አንድ የሩሲያ ሕግ አውጪን ጠቅሶ የዘገበው ኢንተርፋክስ የዜና ወኪል “የሆነ ነገር ጠብቁ” ብሏል፡፡
ኢንተርፋክስ እንደዚህ ቢልም ሞስኮ ግን ጉዳዩን ቀልል አድርጋ ያየችው ነው የሚመስለው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስርያ ቤቷ ‘አለው’ ተብሎ እንደወጣው መረጃ ከሆነ ሞስኮ በተባለው ነገርና በተወሰደው እርምጃ አዝናለች፡፡ ሆኖም “የሁለትዮሽ ግንኙነቱ አይበላሽም” የሚል ተስፋ እንዳላት ተነግሯል፡፡
የፕሬዝዳንት ፑቲን መንግስት ስለ ጉዳዩ “መረጃው የለኝም” ስለማለቱ ከክሬምሊን የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ነገር ግን ሩሲያ ሃገራቱ “አዎንታዊ እና ገንቢ” ግንኙነታቸውን እንደሚጠብቁ ተስፋ ስለማድረጓ ተጠቁሟል፡፡
ባለፉት ወራት የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያውያን ላይ መሰል ክስ እያቀረቡ ነው፡፡
ቡልጋሪያ እና ኔዘርላድ ባሳለፍነው መጋቢት እንዲሁም ወርሃ ታህሳስ ላይ የሩሲያ ባለስልጣናትን ማባረራቸው የሚታወስ ነው፡፡