በአፍጋኒስታን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ ደረሰ
የታሊባን መሪ ሂባቱላህ አክሁንዝዳ “በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ወድመዋል የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር ይችላል” ብለዋል
አሳዛኝ ክስተቱን ተከትሎ የታሊባን ባለስልጣናት ዓለም አቀፍ እርዳታ በመጠየቅ ላይ ናቸው
በአፍጋኒስታን ረቡዕ እለት በሬክተር ስኬል መጠኑ 6 ነጥብ 1 በሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ መድረሱ የታሊባን ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
ርዕደ መሬቱ ከደቡብ ምስራቅ ክሆስት ከተማ 44 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ተኩል ላይ የተከሰተ ሲሆን በርካታ ሰዎችም ተኝተው በነበረበት ወቅት ላይ ተብሏል።
ምስሎችና ፎቶግራፎች እንደሚያሳዩት በምስራቅ ፓኪቲካ ግዛት የመሬት መደርመስ እና በጭቃ የተሰሩ ቤቶችን እንዲሁም ነፍስ ለማዳን የሚሯራጡ የህይወት አድን ሰራተኞች ያሳያሉ።
የታሊባን መሪ ሂባቱላህ አክሁንዝዳ “በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ወድመዋል የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር ይችላል” ብለዋል።
አደጋው በአፍጋኒስታን ላይ በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ከደረሱ እጅግ አስከፊው የመሬት መንቀጥቀጥ ነው ተብሏል።
የፓኪቲካ ግዛት የመረጃ ሃላፊ መሀመድ አሚን ሀዚፊ እስካሁን ባለው መረጃ 1 ሺህ ሰዎች መሞታቸውን እና 1ሺ 500 መቁሰላቸው ተናግረዋል ።
የነፍስ አድን ቡድኖች አሁንም ከመሬት በታች የተቀበሩ ሰዎችን በማፈላለግ ላይ መሆናቸውንም አክለዋል።
ከገጠመው አሳዛኝ ክስተት ጋር አንጻር የታሊባን ባለስልጣናት ዓለም አቀፍ እርዳታ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ባለስልጠናቱ "በየትኛውም ሀገር እንደዚህ አይነት ትልቅ ክስተት ሲከሰት የሌሎች ሀገራት እርዳታ ያስፈልጋል" ስለዚም የዓለም ድጋፍ ያስፈልገናል የሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአፍጋኒስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ከየትኛውም አለም አቀፍ ድርጅት እርዳታ እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።