አሜሪካ ዜጎቿን ከአፍጋኒስታን የምታስወጣበት የመጨረሻ ዕለት ዛሬ መሆኑን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ገልጸው ነበር
የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን መውጣታቸው ሀገሪቱን ነጻ እና ሉዓላዊ እንዳደረጋት ካቡልን ከተቆጣጠረ ሁለት ሳምንት የሞላው ታሊባን አስታወቀ፡፡
ካቡል በሚገኘው ሃሚድ ካርዛይ አውሮፕላን ማረፊያ ሆነው መግለጫ የሰጡት የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢ ሁላህ ሙጃሂድ የቡድናቸው ድል የሁሉም ደስታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ እስላሚክ ኢሚሬትስ ኦፍ አፍጋኒስታን ነጻ እና ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን አንጠራጠርም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ በአፍጋኒስታን ያደረገችውን ወታደራዊ ተልዕኮ እንዳላሳካችም የታሊባን ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡ ቃል አቀባዩ አፍጋኒስታን ከምዕራባውያን ጋር የውጭ ግንኙነት ሥራ እንደምትጀምርም ተናግረዋል፡፡
ሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት የምትጀምረው የአፍጋኒስታንን ነጻነት እና እስላማዊ እሴቶችን ከሚጠብቁ ሀገራት ጋር እንደሆነም ነው የተጠቀሰው፡፡ አሜሪካ ዜጎቿን ከአፍጋኒስታን የምታስወጣበት የመጨረሻ ዕለት ዛሬ መሆኑን ፕሬዝዳንት ባይደን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የመጨረሻዎቹ ሶስት የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ካቡል ከሚገኘው ሐሚድ ካርዛይ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት አፍጋንን ለቀው መውጣታቸው ተዘግቧል፡፡ ይህም ታሊባንን እንዳስደሰተው የተገለጸ ሲሆን አሁን ላይ ሀገሪቱ ነጻነቷን ማወጇን አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ትናንትና ምሽት በአፍጋኒታን ጉዳይ ስብሰባ አድርጎ እደነበር አስታውቋል፡፡ በዚህ ሰብሰባ ላይም፤ ታሊባን አፍጋኒስታንን ለቀው መውጣት ለሚፈልጉ ዜጎች ምቹ የመተላለፊያ ሁኔታ እንዲፈጥር፤ ለሀገሪቱ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲዳረስ፤ የሴቶችንን እና ህጻናትን ጨምሮ ሁሉም ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
15 አምባሳደሮች ይህንን ውሳኔ ሃሳብ ሲደግፉ ቻይናና ሩሲያ ድጋፍም ተቃውሞም አለማቅረባቸው ተገልጿል፡፡ የውሳኔ ሃሳቡ አፍጋኒስታን የሽብርተኝነት መደበቂያ መሆን እንደሌለባትም የሚገልጽ ይዘት እንዳለው ተገልጿል፡፡