በሱዳን ኤል ፋሽር እየተከናወነ በሚገኝው ከፍተኛ ወግያ የሟቾች ቁጥር 134 መሻገሩ ተሰማ
በሁለቱ ጄነራሎች መካከል በሰሜናዊ ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል ፋሽር ጠንከር ያለ ውግያ እየተደረገ ነው
ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን በአካባቢው በሚገኝው ጦርነት እስካሁን 979 ሰዎች እንደተጎዱ ይፋ አድረጓል
በዩክሬን እና ሩስያ እንዲሁም በሀማስ እና በእስራኤል መካከል የሚደረገው ጦርነት ሸፍኖት የተዘነጋ የሚመስለው የሱዳን ጦርነት እያስከተለ የሚገኝው ጉዳት እየጨመረ ነው፡፡
በመከላከያ ስራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መካከል ከሁለት ሳምንታት በፊት በሰሜናዊ ዳርፉር ዋና ከተማ ኤለ ፋሽር በመካሄድ ላይ በሚገኝው መጠኑ ከፍ ያለ ወግያ የሞቱ ንጹሀን ቁጥር ከ134 ተሻግሯል፡፡
ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በአካባቢው ያለው ውግያ ለዜጎች እና ለእርዳታ ድርጅት ሰራተኞች አስቸጋሪ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከሞቱ ሰዎች በተጨማሪ 979 ሰዎች ክፉኛ ጉዳት እንዳጋጠማቸው የገለጸው ቡድኑ እስካሁን ከ500ሺህ የሚልቁ የከተማዋ ነዋሪዎች ከአካባቢው ተፈናቅለዋል ነው ያለው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሌሎች የዳርፉር ግዛቶች ተፈናቅለው የመጡ ዜጎችም አካባቢውን ለቀው በድጋሚ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተሰደዱ ነው፡፡
የሄሚቲ ጦር አርኤስኤፍ በአሁኑ ወቅት 4 የዳርፉር ግዛቶችን ተቆጣጥሮ የሚገኝ ሲሆን በገባባቸው ቦታዎች በሰበአዊ መብት ጥሰት እና በንጹሀን ላይ በሚደርስ ጥቃት በተደጋጋሚ ይወቀሳል፡፡
በሱዳን ከፍተኛ የሆነ ምግብ ፣መድሀኒት እና ሌሎች አስፈላጊ የሰበአዊ ድጋፎች እጥረት ስለመኖሩ ሲነገር፣ የአለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ በዳርፉር ግዛት ብቻ 1.7 ሚልየን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ በሚያስፈልገው ርሀብ ውስጥ ይገኛሉ ብሏል፡፡
በሱዳን በሚያዝያ 2023 በሁለቱ ጄነራሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በአስከፊነቱ የቀጠለ ሲሆን፤ ለ8.8 ሚልየን ሱዳናዊያን ከቀያቸው መፈናቀል ምክንያት ነው፣ 24.8 ሚልየን የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ አስቸኳይ እርዳታን የሚሹ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ደርጅት ዘር ማጥፋት መከላከል ልዩ አማካሪ በባለፈው ሳምንት ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት በሱዳን የዘር ማጥፋት ሊፈጸም የሚችልበት እድል መኖሩን አደጋውም በየቀኑ እየጨመረ እንደሚገኝ አስጠንቅቋል፡፡
በመጪው ሰኔ አንድ የሚጀምረውን የአለም ጤና ጉባኤ አስመልክተው ንግግር ያደረጉት የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው በሱዳን እና ጋዛ ያለው ውግያ መባባስ ሊታከም በሚችሉ ጉዳቶች ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎችን ቁጥር ጨምሮታል ማለታቸው ይታወሳል፡፡