ኬንያ በሚቀጥሉት 3 ሳምንታት ውስጥ የፖሊስ ሀይሏ በሃይቲ እንደሚሰማራ አስታወቀች
ለተደጋጋሚ ግዜ ሲራዘም የነበረው የፖሊስ ሀይሉ ስምሪት ለተጨማሪ ሶስት ሳምንታት ተራዝሟል
ናይሮቢ በሀይቲ የቀጠለውን ወንጀል ለመከላከል አንድ ሺህ ፖሊሶችን ለመላክ ቃል ገብታለች
ኬንያ በሚቀጥሉት 3 ሳምንታት ውስጥ የፖሊስ ሀይሏ በሃይቲ እንደሚሰማራ አስታወቀች
በ2021 የሃይቲ ፕሬዝዳንት ጆቬኔል ሞይስ መገደልን ተከትሎ የተቀሰቀሰው የቡድን ወንጀል፣ ግድያ፣ ዝርፍያ እና ሌሎችም ወንጀሎች ዋና ከተማዋን ፖርት ኦ ፐሪንስን የወንጀል ማዕከል አድርጓታል፡፡
ኬንያ በሃይቲ በአደጋኛ ሁኔታ የጨመረውን የቡድን ወንጀል ለመከላከል ከሀገራት የተውጣጣውን የፖሊስ ሀይል ለመምራት እየተጠበቀች ነው፡፡
ሀገሪቷ ወደ ስፍራው እልከዋለሁ ያለቸው የፖሊስ ሀይል ተልዕኮ በተለያየ ግዜ ሲራዘም ቆይቷል፡፡ ከአንድ አመት በፊት የፖሊስ ሀይሏን ወደ ስፍራው ለመላክ ቃል የገባችው ናይሮቢ እስካሁን ያለቸውን መተግበር አልቻለችም፡፡
ፖሊሶቹ ለመጨረሻ ግዜ በሀይቲ ይደርሳሉ ተብሎ የተጠበቀው ባሳለፍነው ሀሙስ ነበር፡፡
ከሰሞኑ በአሜሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሲያደርጉ የነበሩት ፕሬዝዳንት ሩቶ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ከመከሩባቸው ጉዳዮች መካከል በሀይቲ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እና የኬንያ ፖሊሶች በስፍራቸው ስለሚኖራቸው ሚና የተወያዩበት ይገኝበታል፡፡
ከ15 አመታት ወዲህ በአሜሪካ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የመጀመርያው የአፍሪካ መሪ የሆኑት ሩቶ በብድር እፎይታ ፣ በኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሱዳን ጉዳይ ከነጩ ቤት አለቃ ጋር መክረዋል፡፡
በሶስት ቀኑ የአሜሪካ ጉብኝታቸው ማብቂያ ላይ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሩቶ በሀይቲ ጉዳይ የተቀየረ አቋም አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በስፍራው ከሀይቲ የጸጥታ ሀይል ጋር በጉዳዩ ላይ የሚመክር ልኡክ መላካቸውን ነው ያነሱት፡፡
‘’በስፍራው የሚገኝው የኬንያ ልዑክ የፖሊስ መሰረተ ልማቶች፣ የወንጀል ቡድኖች በስፋት የሚንቀሳቀሱባቸው ስፍራዎች እና ከሌሎች ሀገራት ከሚመጡ ፖሊሶች ጋር በምን መልኩ በጋራ እንደምንሰራ እየመከረ ነው’’ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከተለያዩ ሀገራት የሚውጣጡ ፖሊሶች የሚሰፍሩበት የጦር ካምፕ ግንባታ 70 በመቶ መጠናቀቁን ይፋ አድርገዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሩቶ መንግስት የፖሊስ ጦሩን ወደ ሃይቲ የመለክ ህጋዊ መሰረት የለውም በሚል ያቀረቡትን ክስ ለመመልከት በመጪው ሰኔ ሁለት ቀጠሮ ይዟል፡፡
በጉዳዩ ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው ሩቶ ሀገራቸው ሰላም አስከባሪ ሀይል ስታሰማራ ይህ ለመጀመርያ ግዜ አለመሆኑን ጠቅሰው ሶማሌያ እና ዲ አር ኮንጎን ጨምሮ በ15 አለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ እየተሳተፍን ነው ብለዋል።
ከሰሞኑ ከኔቶ አባልነት ውጭ ያለች ሌላኛዋ የአሜሪካ አጋር በመሆን የተካተተችው ኬንያ አሜሪካ በቀጠናው በሚኖራት የተለያዩ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች ላይ አጋር ስትሆን ይህም ዘመናዊ የአሜሪካ የጦር መሳርያዎች ባለቤት እንድትሆን የሚያደርጋት ነው ተብሏል፡፡