እስራኤል በሀማስ ላይ "ሙሉ ድል" ትቀዳጃለች ብለው እንደማያምኑ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ተናገሩ
እንደጋዛ የጤና ባለስልጣናት ከሆነ እስራኤል እየወሰጀች ባለው መጠነሰፊ ጥቃት ከ35ሺ በላይ ፍልስጤማውያንን ተገድለዋል
የባይደን አስተዳደር እስራኤል በሀማስ ላይ "ሙሉ ድል" ብሎ እንደማያስብ የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኩርት ካምቤል ተናግረዋል
እስራኤል በሀማስ ላይ "ሙሉ ድል" ትቀዳጃለች ብለው እንደማያምኑ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ተናገሩ።
የባይደን አስተዳደር የእስራኤል በሀማስ ላይ "ሙሉ ድል" የመቀዳጀት ጉዳይ ይሳካል ብሎ እንደማያስብ የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኩርት ካምቤል ሰኞ እለት ተናግረዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት እስራኤል ከጦርነቱ በኋላ የጋዛን አስተዳደር ሁኔታ የሚያመላክት ገልጽ ፍኖተ ካርታ እንድታዘጋጅ ለመርዳት ፍላጎታቸው ቢገልጹም፣ የካምቤል አስተያየት ግን እስራኤል አሁን በያዘችው ወታደራዊ ዘመቻ ያለመችውን ግብ መምታት አንደማትችል ማመናቸውን የሚያሳይ ነው ተብሏል።
"አንዳንዴ፣ ድል ምንድነው እያልን እንሟገታለን" ሲሉ ካምቤል በሚያሚ በተደረገ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
"የእስራኤል መሪዎችን በቅርበት ስንሰማቸው ብዙ ጊዜ የሚያወሩት ስለአጠቃላይ ድል ነው።"
"ይህ የሚሆን ነው ብለን ማመን አለብን ብየ አላስብም፤ ሁኔታው እኛ ከ9/11 ጥቃት ካጋጠመን ጋር በብዙ መልኩ ይመሳሰላል"ብለዋል ከምቤል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ጥቅምት ወር ጥቃት አድርሶ 1200 ሰዎችን ገድሎ እና ሌሎች 250 ሰዎች አግቶ በወሰደው ሀማስ ላይ "ሙሉ ድል" መቀዳጀት እንደማፈልጉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
እንደጋዛ የጤና ባለስልጣናት ከሆነ እስራኤል እየወሰጀች ባለው መጠነሰፊ ጥቃት ከ35ሺ በላይ ፍልስጤማውያንን ተገድለዋል።
ካምቤል ይህን አስተያየት የሰጡት እስራኤል የዋሽንግተንን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት በጋዛ ደቡባዊ ጫፍ የምትገኘውን የራፋ ከተማ ማጥቃቷን በቀጠለችበት ወቀት ነው።
በጋዛ ያለውን ሁኔታው የ9/11 ጥቃትን ተከትሎ አሜሪካ ኢራቅን እና አፍጋኒስታንን ከወረረች በኋላ ካጋጠማት ጋር ያመሳሰሉት ባለስልጣኑ ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልጋል ብለዋል።
"እኔ እንደሚመስለኝ ከሆነ ፖለቲካዊ መፍትሄ መኖር አለበት። አሁን ላይ ብዙ ሀገራት የፍልስጤማውያን መብቶች የሚጠበቁበት የፖለቲካ መፍትሄ እንዲመጣ ይሻሉ።"
በቅርቡ ሀማስ አደራዳሪዎቹ ግብጹ እና ኳታር ያቀረቡትን ሶስት ምዕራፍ ያለው የተኩስ አቁም እቅድ ተቀብሎት ነበር። ነገርግን እስራኤል የምትፈልጋቸው ቅደመ ሁኔታዎች አለመሟላታቸውን በመግለጽ እቅዱን አልተቀበለችውም።