እስራኤል ማጥቃቷን ብትቀጥልም፣ ሶሪያን የተቆጣጠረው ቡድን መሪ ወደ ግጭት የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ገለጸ
የቡድኑ መሪ ሀገሪቱ በመልሶ ግንባታ ላይ ስለምታተኩር ወደ አዲስ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌላት በትናንትናው ተናግሯል
ሳኡዳ አረቢያ፣ አረብ ኢምሬትስ እና ጆርዳንን ጨምሮ በርካታ የአረብ ሀገራት እስራኤል በጎላን ተራሮች ያለው ከጦር ነጻ ቀጣና ቦታ መቆጣጠሯን አውግዘዋል
እስራኤል ማጥቃቷን ብትቀጥልም፣ ሶሪያን የተቆጣጠረው ቡድን መሪ ወደ ግጭት የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ገለጸ።
ሶሪያን የተቆጣጠረው ቡድን መሪ የሆነው አህመድ አልሻዓራ እስራኤል እየፈጸመች ያለውን ጥቃት ምክንያታዊ ለማድረግ የውሸት ሰበቦችን እየተጠቀመች ቢሆንም ሀገሪቱ በመልሶ ግንባታ ላይ ስለምታተኩር ወደ አዲስ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌላት በትናንትናው ተናግሯል።
አቡ መሀመድ አል ጎላኒ በሚል ስም የሚታወቀው አህመድ ሻዓራ ለአምስት አስርት አመታት ሶሪያን ያስተዳድረውን የበሽር አላሳድ ቤተሰባዊ አገዛዝን የገረሰሰው የሀያት ታህሪ አልሻም መሪ ነው።
እስራኤል፣ ከ1973 አረብ-እስራኤል ጦርነት በኋላ የተፈጠረውን ከጦር እንቅስቃሴ ነጻ ቀጣናን ወይም 'ዲሚሊታራይዝድ ዞን' ጨምሮ ደማስቆን ከላይ ወታደች ማየት የሚቻልበትን የሄርሞን ተራራን ተቆጣጥራለች።
ቦታዎችን ተቆጣጥሮ የመቆየት ፍላጎት እንደሌላት የምትገልጸው እስራኤል በመላው ሶሪያ ውስጥ ያሉ ሚሳይሎች፣ ሮኬቶችና ኬሚካሎች ጨምሮ ስትራቴጂካዊ የጦር መሳሪያዎች በአባሪዎች እጅ እንዳይገቡ በሚል እያወደመች ነው።
ሳኡዳ አረቢያ፣ አረብ ኢምሬትስ እና ጆርዳንን ጨምሮ በርካታ የአረብ ሀገራት እስራኤል በጎላን ተራሮች ያለው ከጦር ነጻ ቀጣና ቦታ መቆጣጠሯን አውግዘዋል።
"የእስራኤል መከራከሪያ ደካማ እና በቅርቡ የፈጸመችውን ጥቃት ምክንያታዊ የማያደርግ ነው። እስራኤል ከጦር ነጻ የሆነውን ቀጣና በመጣስ በቀጣናው ፍጥጫ እንዲኖር ስጋት ደቅናለች" ሲል አልሻራ ሶሪያ ቴሌቪዥን በተባለው የተቃዋሚዎች ሚዲያ ቀርቦ ተናግሯል።
"በጦርነት የተጎዳችው ሶሪያ ሁኔታ ለአዲስ ፍጥጫ ዝግጁ አይደለም።በዚህ ወቅት ትኩረት የሚሰጠው ተጨማሪ ውድመት የሚያመጣ ሳይሆን መልሶ ግንባታ እና መረጋጋት ነው" ብሏል ሻዓራ።
ሻራ አክሎም እንደገለጸው ደህንነት ለማስከበር እና መረጋጋት ለመፍጠር የሚያስችለው ብቸኛ አማራጭ ንግግር ነው።
ለአስርት አመታት ወታደሮቿን ሶሪያን ውስጥ በማሰማራት አሳደን ሰትደግፍ የነበረችውን እና በመጨረሻም ጥገኝነት የሰጠችውን ሩሲያን በተመለከተ፣ ሻራ ከሶሪያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት የጋራ ጥቅምን ባከበረ መልኩ መሆን አለበት ብሏል።