የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በሶሪያ በኩል ያለው የአቅርቦት መስመሩ እንደተቋረጠበት ገለጸ
ከ50 አመታት በላይ የቆየው የአሳድ ቤተሰባዊ አስተዳደር የቀድሞ አልቃ ኢዳ አጋር በነበረው ሀያት ታህሪር አል ሻም በሾመው ባለአደራ አደራ መንግስት ተተክቷል
ሄዝቦላ "እነዚህን አዲስ ኃይሎች" አሁን ላይ እንዲህ ናቸው ብሎ መወሰን እንደማይችል ገልጿል
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በሶሪያ በኩል ያለው የአቅርቦት መስመሩ እንደተቋረጠበት ገለጸ።
የሄዝቦላ መሪ ኔይም ቃሲም የሶሪያ ፕሬዝደንት በሽር አል አሳድ ከስልጣን ከተወገዱ ከአንድ ሳምንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው አስተያየት በሶሪያ በኩል ያለው የአቅርቦት መስመር እንደተቋረጠበት ገልጿል።
በሽር አል አሳድ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላ የጦር መሳሪያዎችን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በኢራቅ እና በሶሪያ በኩል በማድረግ ወደ ሊባኖስ ለማስገባት ሶሪያን ይጠቀም ነበር።
ነገርግን ባለፈው ታህሳስ 6፣2024 ጸረ-አሳድ አማጺያን ከኢራቅ ጋር ያለውን ድንበር በመቆጣጠር የአቅርቦት መስመሩን የቆረጡ ሲሆን ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ ዋና ከተማዋን ደማስቆን ተቆጣጥረዋል።
"አዎ፤ በአሀኑ ወቅት ሄዝቦላ በሶሪያ በኩል ያለውን የአቅርቦት መስመር አጥቷል" ሲሉ ቃሲም በቴሌቪዥን በተላለፈው መግለጫ ተናግረዋል። ቃሊም አክሎም "አዲስ አስተዳደር ሲመጣ ይህ መስመር ወደ ነበረበት ሊመለስ ይችላል፤ ሌላ አማራጭም ልንፈልግ እንችላለን" ብሏል።
በ2013 ሄዝቦላ አሳድ እየተዋጉት የነበሩትን አማጺያንን እንዲያሸንፍ ድጋፍ ለማድረግ ጣልቃ ገብቶ ነበር። ባለፈው ሳምንት አማጺያኑ ወደ ደማስቆ ሲጠጉ ተዋጊዎቹን ለማስወጣት የሚያመቻቹ ኃላፊዎችን መላኩን አሳውቆ ነበር።
ከ50 አመታት በላይ የቆየው የአሳድ ቤተሰባዊ አስተዳደር የቀድሞ አልቃ ኢዳ አጋር በነበረው ሀያት ታህሪር አል ሻም በሾመው ባለአደራ አደራ መንግስት ተተክቷል።
ሄዝቦላ "እነዚህን አዲስ ኃይሎች" አሁን ላይ እንዲህ ናቸው ብሎ መወሰን እንደማይችል የገለጸው ቃሲም የሊባኖስ እና ሶሪያ ህዝቦች ግን በመተባበር እንዳለባቸው አምናለሁ" ብሏል።
"አዲሱ ገዥ ፓርቲ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት እንደማያድስ እና ጠላት ብሎ ይፈረዳታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ እነዚህ ናቸው በእኛ እና በሶሪያ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚወስኑት" ብሏል ቃሲም።
ሄዝቦለ እና እስራኤል በጋዛ ጦርነት ምክንያት ለአንድ አመት ያህል በድንበር ላይ የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ እስራኤል ባለፈው መስከረም ሊባኖስን ድንበር በመጣስ በእግረኛ ጦር እና በአየር ኃይል መጠነሰፊ ጥቃት አድርሳለች።