ምርመራ የተከፈተባቸው ፕሬዝደንት ለአቃቤ ህግ ትዕዛዝ ተገዥ አልሆኑም ተባለ
ዩን ባወጁት ወታደራዊ አዋጅ ምክንያት በትናትናው እለት ከስልጣን ታግደው ፕሬዝደንታዊ ኃላፊነቶችን እንዳይወጡ ተደርገዋል
ዩን አመጽ በመቀስቀስና ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ሊያስከስስ በሚችል ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል
ባወጁት ወታደራዊ አዋጅ ወይም ማርሻል ሎው ምክንያት ከስልጣን የተነሱት እና ምርመራ የተከፈተባቸው የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ዩን ሱክ የኦል ለአቃቤ ህግ ትዕዛዝ አልገዛ ማለቻቸው ተነግሯል።
ዩን በመጀመሪያ ጥሪ ባለመገኘታቸው ምክንያት ምርመራ እያካሄደባቸው ያለው አቃቤ ህግ ለሁለተኛ ጊዜ መጥሪያ ሊሰጣቸው መሆኑን ሮይተርስ የደቡብ ኮሪያውን የዜና አገልግሎት ዮንሃፕን ጠቅሶ ዘግቧል።
ዩን እና ሌሎች በርካታ ከፍተኛ ባለስጣናት አመጽ በመቀስቀስ፣ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም እንዲሁም ህዝብ መብቱን እንዳይጠቀም በመከልከል ሊያስከስስ በሚችል ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል።
በዩን ያልተሳካ ወታደራዊ ህግ አዋጅ ላይ ምርመራ እያካሄደ ያለው ልዩ የአቃቤ ህግ ቡድን ዩን ባለፈው ረብዕ እለት (በሀገሪቱ ሰአት አቆጣጠር ከጠዋቱ 4:00) ለጥያቄ እንዲቀርቡ የሚጠይቅ መጥሪያ ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም ሳይገኙ ቀርተዋል።
አቃቤ ህጉ ለፕሬዝደንት ዩን ሌላ መጥሪያ ለማዘጋጀት ማቀዱን ዘገባው ጠቅሷል።
ዩን ባወጁት ወታደራዊ አዋጅ ምክንያት በትናትናው እለት ከስልጣን የተነሱ ሲሆን ፕሬዝደንታዊ ኃላፊነቶችን እንዳይወጡ ታግደዋል።
አቃቤ ህግ በዛሬው እለት የስፔሻል ጦር አዛዡን ጨምሮ ከፍተኛ የጦር ባለስልጣናትን ለመያዝ የእስር ማዘዣ እየፈለገ ነው ተብሏል።
በሌላ በኩል ፖሊስ ዩን ወታደራዊ ህግ ባወጁበት ወቅት 1500 ወታደሮች ተሰማርተው ነበር ብሏል።