አሜሪካ አሳድን ካስወገደው የሶሪያ አማጺ ቡድን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረጓን ብሊንከን አስታወቁ
የታጣቂ ቡድኖችን ጥምረት የመራው ሀያት ታህሪር አል ሻም ባለፈው ሳምንት አሳድ ከስልጣን እንዲወርድ እና ወደ ሩሲያ እንዲሰደድ አድርጎታል
ብሊንከን ከስምንት የአረብ ሀገራት እና ቱርክ ጋር በመሆን ሶሪያን ወደ ሰላማዊ፣ በሀይማኖት ያልተከፋፈለች እና አካታች ሀገር እንድትሆን ያስችላል በተባለው መርህ ላይ ፈርመዋል።
አሜሪካ አሳድን ካስወገደው የሶሪያ አማጺ ቡድን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረጓን ብሊንከን አስታወቁ ።
የአሜሪካ ባለስልጣናት የሶሪያውን ፕሬዝደንት በሽር አል አሳድን ከስልጣን ካስወገደው በሽብር ከተፈረጀው አማጺ ቡድን ጋር ቀጥተኛ ንግግር ማድረጋቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትናንትናው እለት አስታውቀዋል።
የታጣቂ ቡድኖችን ጥምረት የመራው ሀያት ታህሪር አል ሻም(ኤችቲኤስ) ባለፈው ሳምንት አሳድ ከስልጣን እንዲወርድ እና ወደ ሩሲያ እንዲሰደድ አድርጎታል።
ብሊንከን ከስምንት የአረብ ሀገራት እና ቱርክ ጋር በመሆን ሶሪያን ወደ ሰላማዊ፣ በሀይማኖት ያልተከፋፈለች እና አካታች ሀገር እንድትሆን ያስችላል በተባለው መርህ ላይ ፈርመዋል።
ከኤችቲኤስ ጋር ስላደረጉት ንግግር በዝርዝር መናገር ያልፈለጉት ብሊንከን አሜሪካ ሽግግሩ እንዴት እንዲመራ እንደምትፈልግ ማሳወቅ አስፈላጊ ነበር ብለዋል።
"አዎ፤ ከኤችቲኤስ እና ከሌሎች አካላት ጋር ንግግር አድርገናል" ብለዋል ብሊንከን።ብሊንከን አክለውም "ለሶሪያ ህዝብ ያለን መልእክት ይህ ነው፦ እንዲሳካላቸው እንፈልጋለን፤ ለዚህም ልንረዳቸፍ ዝግጁ ነን።" ብለዋል።
በአንድ ወቅት የአልቃ ኢዳ አጋር የነበረው ኤችቲኤስ ከ2018 ጀምሮ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሽብርተኝነት ተፈርጆ ነበር።ፍረጃው ቡድኑ እና የቡድኑ አባላት ምንም አይነት እርዳታ እንዳይደርሳቸው ማድረግን ጨምሮ ከባድ ማዕቀብ ተጥሎበት ቆይቷል።
ከአሜሪካ በተጨማሪ ቱርክ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ተመድ ኤችቲኤስን በሽብር ፈርጀውታል።
አማጺያኑ አሁን ላይ ጊዜያዊ የባለአደራ መንግስት አቋቁመዋል።
የሶሪያ አማጺያን ለ 50 አመታት የቆየውን የአሳድ ቤተሰባዊ አስተዳደር በጥቂት ቀናት ውስጥ በፈጸሙት መብረቃዊ ጥቃት መገርሰስ መቻላቸው፣ በመካከለኛው ምስራቅ ጉልህ ክትተት ሆኖ ተመዝግቧል።