አስከሬናቸውን ሳያገኙ ቁፋሮ እንደማያቆሙ በደላንታ ወረዳ መሬት ውስጥ የተቀበሩ ወጣቶች ቤተሰቦች ተናገሩ
በደላንታ ወረዳ ማዕድን በማውጣት የነበሩ ወጣቶች መሬት ውስጥ ከተቀበሩ 36 ቀን ሆኗቸዋል
መሬት ውስጥ ከተቀበሩት ወጣቶች ውስጥ የሶስቱ ሚስቶቻቸው ነፍሰጡሮች ሲሆኑ ከባድ ጊዜ እያሳለፉ እንደሆነ ተገልጿል
አስከሬናቸውን ሳያገኙ ቁፋሮ እንደማያቆሙ በደላንታ ወረዳ መሬት ውስጥ የተቀበሩ ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ፡፡
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ 018 ቀበሌ ልዩ ስሙ አለኋት ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ነበር ኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ የነበሩ ወጣቶች መውጫቸው በአለት የተደፈነባቸው፡፡
ኦፓል ማዕድን በማውጣት ስራ የተደራጁ ወጣቶቹ ጥር 29 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት ላይ በቁፋሮ ላይ እያሉ እንደተናደባቸው የማህበሩ ቡድን መሪ መኳንት ለጌ ለአልዐይን ተናግሯል
እንደ መኳንት ገለጻ ከሆነ “ዘጠኝ ወጣቶች አዳራቸውን ኦፓል ማዕድን ለማውጣት እየቆፈሩ እያለ መውጫ በራቸው በአለት ተደፍኖባቸዋል፡፡”
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአካባቢው ህዝብ፣ ቤተሰቦቻቸው እና የመንግስት ተቋማት ወጣቶቹን በህይወት ለመታደግ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ይሁንና ቦታው አለታማ እና ለመረዳዳት አስቸጋረ በመሆኑ ምክንያት የተደረገው ጥረት ውጤታማ እንዳልሆነ የሚናገው መኳንት አሁን ላይ መንግስት እና የአካባቢው ማህበረሰብ ጥረታቸውን ሙሉ ለሙሉ ማቋረጣቸውን አክሏል፡፡
መሬት ውስጥ የተቀበሩ ወጣቶች ቤተሰቦች ግን ልጆቻቸው በህይወት ባያገኙ እንኳን ቢያንስ አስከሬናቸውን፣ እንዴት ሆነው ህይወታቸው አለፈ የሚለውን ለማወቅ ቁፋሮውን እንደቀጠሉ ነግሮናል፡፡
እድሜያቸው ከ17 እስከ 25 የሚደርሱት እነዚህ ወጣቶች አራቱ ትዳር መስርተዋል የተባለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የሶስቱ ወጣቶች ሚስቶች ነፍሰ ጡር ወይም እርጉዝ እንደሆኑ፣ ከሟቾች መካከል አንዱ የእህቱ ባል እንደሆነም መኳንት ተናግሯል፡፡
አደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡት ሁሉ ከባድ ቢሆንም በተለይ ነፍሰ ጡር የሆኑት ሴቶች በባሎቻቸው ሁኔታ አስቸጋሪ ጊዜ እያሳለፉ መሆኑን የነገረን መኳንት ምን አልባት በተዓምር በህይወት ሊገኙ ይችሉ ይሆናል የሚል ትንሽዬ ተስፋ እንዳላቸውም አክሏል፡፡
እነዚህ ነፍሰ ጡር ሴቶች ህይወታቸውን የሚመሩት ከባሎቻቸው በሚያገኟት ትንሽዬ ገቢ ነበር አሁን ባሎቻቸው መሬት ውስጥ ተቀብረው በመቅረታቸው ባንድ በኩል ሀዘኑ በሌላ በኩል ደግሞ ችግሩ እያሰቃያቸው እንደሆነም ሰምተናል፡፡
“ቁፋሮው አንድ ዓመት ቢፈጅም እንኳን የልጆቹ አስከሬን ሳናገኝ ቁፋሯችንን አናቆምም” ያለው መኳንት ለጌ “እስካሁን 80 ሜትር ድረስ እንደተቆፈረ ገልጾ ወጣቶቹ የተቀበሩት 150 ሜትር ላይ እንደሆኑ አውቃለሁ” ብሎናል፡፡
ጥር 23 ቀን 2016 ዓም ላይ እኔ እና አንድ ሌላ ወጣት እዚህ ቦታ ላይ ኦፓል ለማውጣት እየቆፈርን እያለ ተንዶብን በሌላ አቅጣጫ ቆፍረን ህይወታቸውን እንዳተረፈ በሳምንቱ በዘጠኙ ወጣቶች ላይ ይህ ክስተት ሊፈጠር እንደቻለም ነግሮናል፡፡
ቦታውን እኛ በደንብ እናውቀዋለን የሚለው መኳንት ልጆቹ ከተቀበሩበት ቦታ ለመድረስ 70 ሜትር ያህል እንደሚቀራቸው ነግር ግን ያሰብነውን እንድናሳካ እና የወጣቶችን አስከሬን አግኝተን በክብር መቅበር እንድንችል የቁፋሮ ባለሙያዎች አልያም ከዚህ ጋር የተያያዙ መሳሪያዎች ያላቸው ሰዎች እንዲረዷቸውም ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግስት ልጆቹን በህይወት ለማውጣት የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር በሰው ሀይል ጉልበት እንዲቆፈር፣ ጥረቱን ለማፍጠን ደግሞ ታንክ እና ፈንጂ ሳይቀር አቅርቦ ሲረዳቸው እንደነበር፣ ይሁንና ግን ጥረቱ ሁሉ እንዳልተሳካ ገልጿል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ኦፓል ማዕድን በማውጣት ስራ ላይ የነበሩ 11 ወጣቶች ተመሳሳይ አደጋ አጋጥሟቸው ነበር የተባለ ሲሆን ከሁለት ሳምንት እልህ አስጨራሽ ቁፋሮ በኋላ አራቱን ወጣቶች በህይወት ማግኘት ተችሎ እንደነበር የደቡብ ወሎ ኮሙንኬሽን መምሪያ ከዚህ በፊት መናገሩ ይታወሳል፡፡