አማኞቹ ለቀድሞው ፕሬዝዳንት የተለየ ጥበቃ ይደረግለት ዘንድ “አምላካቸውን” ጠይቀዋል ነው የተባለው
በህንድ ዋና ከተማ የሚገኙ የሂንዱ እምነት ተከታዮች ለቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለ7 ቀናት የሚቆይ የጸሎት ስነስርአት ጀምረዋል።
“ሂንዱ ሲና” በመባል የሚታወቁት እነዚህ ቡድኖች ትራምፕ ፖለቲካውን ከተቀላቀሉበት 2016 ጀምሮ በየአመቱ የልደት ቀኑን አስታውሰው ያከብራሉ።
ከሰሞኑ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ የሰሙት አማኞቹ “የሀይል እና ጥበቃ ጌታ” በሚል በሚጠሩት “ባግላሙኪ” ከተሰኝው የሂንዱ አምላክ ምስል ከፍ ብሎ ረጂም እድሜ ለትራምፕ የሚል ጽሁፍ ያረፈባቸውን የዶናልድ ትራምፕ ፎቶዎችን በመስቀል ሀይማኖታዊ ስርአትን አከናውነዋል።
የጸሎቱ መሪው የአምልኮ ስርአቱን ባከናወኑበት ወቅት አምላካቸው ለትራምፕ ጥበቃ እና ደህንነትን እንዲያወርድለት ጠይቀዋል ሲል ሮይተርስ ነው ያስነበበው።
ዛሬ እንደተጀመረ የተሰማው የአምልኮ እና ጸሎት ስነስርአቱ የትራምፕ ደህንነት እና ጤንነት ላይ በማተኮር ለቀጣዮቹ ስድስት ቀናት ይዘልቃል ተብሏል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ወደ አሜሪካ ፖለቲካ ብቅ ካሉበት ወቅት ጀምሮ በአንድ ላይ በመሰባሰብ ለደታቸውን የሚያከብሩት አማኞች ኬክ ፣ ፊኛዎችን እና የድግስ ኮፍያዎችን በመጠቀም አሜሪካውያን ልደቶችን በሚያከብሩበት መንገድ የትራምፕን ልደት ሲያከብሩ ቆይተዋል፡፡
ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው የሚናገሩት አማኞቹ ለሂንዱ ማህበረሰብ ደህንነት እና እድገት ብቻ ነው የምንሰራው ይላሉ።
200 ሚሊየን የሚጠጉ የእስልምና እመነት ተከታዮች በሚኖሩባት ህንድ የሂንዱ እመነት ተከታዮች በሙስሊሞች እና በመስጂዶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመፈጸም ይታወቃሉ።
የሂንዱ ብሄርተኛ እንደሆነ የሚነገርለት የናሪንድራ ሞዲ ባሃራቲያ ጃንታ ፓርቲ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በሙስሊሞች ላይ የሚደርስ ጥቃት እና ወንጀሎች መጨመራቸው ይነገራል።