ለልጃቸው የቅድመ ሰርግ ድግስ 50 ሺህ ሰዎችን የጠሩት የህንድ ቢሊየነር
የአለማችን ታዋቂ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሪዎች፣ የሆሊውድና ቦሊውድ ኮከቦች እንዲሁም ፖለቲከኞች በግዙፉ ድግስ ላይ ይታደማሉ ተብሏል
የህንድ ቁጥር አንድ ቱጃሩ ሙኬሽ አምባኒ በ2018 ሴት ልጃቸውን ሲድሩ 100 ሚሊየን ዶላር ማውጣታቸው ተገልጿል
ህንዳዊው ቢሊየነር ሙኬሽ አምባኒ በትውልድ ቀያቸው 50 ሺህ ሰዎች የሚታደሙበት ድግስ አዘጋጅተዋል።
ወንድ ልጃቸውን በዚህ አመት የሚድሩት ቢሊየነሩ ለሶስት ቀናት የሚቆይ የቅድመ ሰርግ ድግስ ወይም ፓርቲ ማዘጋጀታቸው ተነግሯል።
አምባኒ በጉጃራት ክልል በምትገኘው ጃምናጋር ከተማ ባዘጋጁት ድግስ ላይ የአለማችን ታዋቂ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ስራ አስፈጻሚዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሆሊውድ እና ቦሊውድ ዝነኞች ይገኛሉ ብሏል ሂንዱስታን ታይምስ።
ነዳጅ እና ቴሌኮምን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች የተሰማራው ሪሊያንስ ኢንዱስትሪስ ባለቤቱ የ66 አመቱ ቢሊየነር ከ114 ቢሊየን ዶላር በላይ ሃብት እንዳለው ፎርብስ ይገልጻል፤ ይህም የእስያ ቁጥር 1 ባለጸጋ ያደርገዋል።
በዚህ አመት የ28 አመት ልጃቸውን አናንት ለ29 አመቷ ነጋዴ ራድሂካ መርቻንት የሚድሩት አምባኒ የሶስት ቀናት ድግሱን በተወለዱበት ቀዬ ያዘጋጁት ደስታቸውን ከቅርቦቻቸው ጋር ለመጋራት ነው ተብሏል።
ቢሊየነሩ ልጄ ለወግ ለማረግ ሊበቃ ነውና አብራችሁን ደስ ተሰኙ ብለው ጥሪ ያቀረቡላቸውን ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ለማስደሰትም ዝግጁ መሆናቸውን በትናንትናው እለት ገልጸዋል።
በ2018 ሴት ልጃቸውን የዳሩት ቢሊየነሩ በህንድ እጅግ ውዱን ሰርግ በመደገስ ይታወቃሉ።
አሜሪካዊቷ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቢዮንሴ የዘፈነችበት ሰርግ 100 ሚሊየን ዶላር ወጪ እንደተደረገበት መገለጹን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አስታውሷል።
በወንድ ልጃቸው የቅድመ ሰርግ ድግስ ወይም ፓርቲ ላይም የአር ኤንድ ቢ ኮከቧ ሪሃናን ጨምሮ ታዋቂ አንቀንቃኞች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።
የማይክሮሶፍት መስራቹ ቢል ጌትስ፣ የሜታ ስራ አስፈጻሚው ማርክ ዙከርበርግ እና የዲዝኒ ሃላፊው ሮበርት ኢገርን ጨምሮ የበርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሃላፊዎች በድግሱ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ፣ የስዊድን እና ካናዳ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮችም የቢሊየነሩ ግብዣ ከደረሳቸው መካከል ይገኙበታል።
የቦሊውድ ኮከቦቹ አሚታብ ባቺቻን እና ሻሃሩክ ካሃንም በሙኬሽ አምባኒ ግዙፍ ድግስ ላይ ይታደማሉ ተብሏል።