በህንድ የተመረዘ አልኮል የጠጡ 34 ሰዎች ህይወት አለፈ
መጠጡን የጠጡ ከ80 በላይ ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸውና የሟቾቹ ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችልም ተገልጿል
በህንድ በቤት ውስጥ የሚሰሩ የአልኮል መጠጦችን ጠንካራ ለማድረግ የሚጨመሩ ኬሚካሎች የበርካቶችን ህይወት ይቀጥፋሉ
በህንድ የተመረዘ አልኮል የጠጡ 34 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተነገረ።
ታሚል ናዱ በተባለው ግዛት ካልካኩሩቺ ከተማ በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጅና የሚሰራጭ አልኮል ከጠጡ በኋላ ተመርዘው ሆስፒታል ገብተዋል ተብሏል።
ከ80 በላይ ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ መሆናቸውም የሟቾቹን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የተመረዘውን አልኮል አከፋፍለዋል የተባሉ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል።
በህገወጥ መንገድ የተመረዘ አልኮል ወደከተማዋ እንዳይገባ መቆጣጠር አልቻሉም በሚልም ከፍተኛ የፖሊስ አዛዥ እና ሌሎች 10 ባለስልጣናት ከስራቸው መታገዳቸው ነው የተገለጸው።
በተመረዘው አልኮል ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች 1 ሚሊየን ሩፒ (12 ሺህ ዶላር) ፤ ተጎድተው ሆስፒታል ለገቡት ደግሞ ለእያንዳንዳቸው 50 ሺህ ሩፒ እንዲከፈላቸው መወሰኑን የታሚል ናዱ ግዛት አስተዳደሪ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የግዛቷ አስተዳደር ህገወጥ የአልኮል ምርትና ዝውውርን መቆጣጠር አልቻለም በሚል የሚቃወሙ አካላት ግን የአልኮል ሽያጭን ለመከታተል የተሾሙት ሚኒስትር ከስልጣናቸው እንዲለቁ እየጠየቁ ነው።
በህንድ በቤት ውስጥ የሚሰሩ የአልኮል መጠጦችን ጠንካራ ለማድረግ የሚጨመሩ ኬሚካሎች የበርካቶችን ህይወት ይቀጥፋሉ።
አልኮል ጠንካራ ጣዕም እንዲኖረውና እንዳይቀዘቅዝ ለማድረግ ሚታኖል የተባለ ኬሚካል ይጨመራሉ።
ይህ ኬሚካል በጥቂቱ የተጨመረበትን መጠጥ መጠጣት የአይነ ስውረነትን ሊያስከትል ይችላል፤ መጠኑ ከፍ ካለም ጉበት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ በአጭር ጊዜ ህይወትን እንደሚቀጥል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የህንዱ ኒውስ ሚኒት ድረገጽ እንዳስነበበው በአልኮል ውስጥ ሚታኖል ሲጨመረ ከባድ የራስ ምታት፣ ማስመለስ፣ ድካም፣ አቅም ማጣት፣ የሆድ ህመም እና አይንን ማቃጠል ያስከትላል።