ኒው ደልሂ የቡድን 20 ጉባኤ በዝንጀሮዎች እንዳይረበሽ እየተዘጋጀች ነው
የህንዷ መዲና የተለያዩ አስፈሪ ምስሎችን እየለጠፈች ሲሆን፥ የዝንጀሮዎችን ድምጽን የሚያስመስሉ ባለሙያዎችንም ለማሰማራት አቅዳለች
በኒው ደልሂ ከ20 ሺህ በላይ ዝንጀሮዎች እንደሚገኙ ይነገራል
የህንድ ዋና ከተማ ኒው ደልሂ ከ10 ቀናት በኋላ የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባን ታስተናግዳለች።
ከተማዋ እንግዶቿን ለመቀበል እያደረገችው ባለው ሽር ጉድ ውስጥ ለአንድ ጉዳይ የተለየ ትኩረት ሰጥታለች፤ ዝንጀሮዎችን ከመሰብሰቢያ አዳራሽ የማራቅ ዘመቻ።
በከተማዋ የተለያዩ አቅጣጫዎች አስፈሪ የዝንጀሮ ምስሎች እና ቅርጾችን እያስቀመጠች ሲሆን፥ የእንሰሳት ድምጽን የሚያስመስሉ የሰለጠኑ ሰዎችንም ለማሰማራት አቅዳለች ተብሏል።
በኒው ደልሂ ከ20 ሺህ በላይ ዝንጀሮዎች እንዳሉና በየአመቱ በአማካይ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በዝንጀሮዎች እንደሚነከሱ የታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ዘገባ ያሳያል።
“ላንገርስ” የሚሰኙት ጥቁር ፊትና ለረጅም ጭራ ያላቸው ዝንጀሮዎች ባህሪያቸው ቁጡ እና ሃይለኛ ናቸው።
በባለሙያዎች ቁጥጥር ካልተደረገባቸውም ጉዳት እንደሚያደርሱ የህንድ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ተቋም ይገልጻል።
እናም ኒው ደልሂ ከፈረንጆቹ መስከረም 8 እስከ 9 2023 የምታስተናግደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ በዝንጀሮዎች እንዳይታወክ ከ30 በላይ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በየሆቴልና ስብሰባ አዳራሹ ተመድበው ይሰራሉ ተብሏል።
የዝንጀሮዎቹን ድምጽ የሚያስመስሉት ባለሙያዎች ዝንጀሮዎቹ እንግዶቹን እንዳይረብሹ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
ዝንጀሮዎቹ ምግብ ፍለጋ ወደ ስብሰባ አዳራሾች እና ሆቴሎች እንዳያንዣብቡም ከተማዋ በየስፍራው የምግብ ማቅረቢያ እያዘጋጀች ነው ተብሏል።
ኒው ደልሂ በፈረንጆቹ 2014 የላንገርስ ድምጽ የሚያስመስሉና ወደ ፓርላማ እና ሌሎች ቢሮዎች እንዳይገቡ የሚያስፈራሩ 40 ባለሙያዎችን ቀጥራ ነበር።
በ2010 የኮመንዌልዝ ጨዋታዎች በከተማዋ ሲደረግም አትሌቶች በእነዚህ ዝንጀሮዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው 38 የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ማሰማራቷን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።